የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ | ንግድ ባንክ እና ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ ለፍጻሜ ደርሰዋል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለቱም አጋማሾች የመጨረሻ ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው ግቦች ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስን 2ለ1 በማሸነፍ ወደ ፍጻሜው ተሸጋግረዋል።

በካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ የግማሽ ፍጻሜ 8፡30 ሲል በሩዋንዳዊቷ ዳኛ አሊኔ ኡሙቶኒ መሪነት በተጀመረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጨዋታ ንግድ ባንኮች ከኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ ጋር በመጨረሻው የምድብ ጨዋታቸው የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ሳይለውጡት ለጨዋታ ቀርበዋል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች እንደ ሌሎች ጨዋታዎች ሁሉ ፈጣን አጀማመር ለማድረግ የሞከሩት ንግድ ባንኮች 4ኛው ደቂቃ ላይ በሴኮንዶች ልዩነት በሴናፍ ዋቁማ እና በንግሥት በቀለ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂዋ ጆሴፊን ናምቡያ ሲመለስባቸው 6ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ መሳይ ተመስገን ከቅጣት ምት ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ታሪኳ ዴቢሶ በግንባር ገጭታ ጥሩ ሙከራ ብታደርግም ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

ረዘም ላሉ ደቂቃዎች እጅግ ቀዝቃዛ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ 44ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ ሙከራ አድርጋ በግብ ጠባቂዋ ከተመለሰባት ከአንድ ደቂቃ በኋላ ግብ አስቆጥረዋል። በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም ንግሥት በቀለ በጥሩ ዕይታ ለመሳይ ተመስገን አመቻችታ አቀብላት መሳይም በተረጋጋ አጨራረስ አስቆጥራው ንግድ ባንክን መሪ አድርጋለች።

ከዕረፍት መልስ የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገው አጋማሹን የጀመሩት ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ቀስ በቀስ ወደ ጠንካራ እንቅስቃሴ በመምጣት 59ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ከሀዲጃህ ናንዳጎ የተነሳው ኳስ በግብ ጠባቂዋ ቢመለስም ሻዲያ ናቢርዬ አግኝታው መረብ ላይ ማሳረፍ ችላለች።

የአቻነት ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በሚያገኙት ኳስ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት ያደረጉት ንግድ ባንኮች መሳይ ተመስገን ከረጅም ርቀት ሞክራው በግብ ጠባቂዋ የተመለሰውን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ ብታስቆጥረውም ከጨዋታ ውጪ ሆኖ ሲሻር ተጨማሪ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም ነበር።

በዝናባማ የዓየር ሁኔታ ታጅቦ ሊጠናቀቅ ተቃርቦ በነበረው ጨዋታ 90ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ ባንኮች አሸናፊ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረዋል። እመቤት አዲሱ ከሳጥን ውጪ የመታችው ኳስ የግብ ጠባቂዋ ስህተት ተጨምሮበት መረቡ ላይ አርፏል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቀደም ብሎ 5 ሰዓት ላይ በተደረገው ጨዋታ ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ 3ለ2 በሆነ ውጤት ሲምባ ኩዊንስን ያሸነፈ ሲሆን ውጤቶቹን ተከትሎም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሐሙስ 8 ሰዓት ላይ ከኬንያ ፖሊስ ጋር የፍጻሜ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።