ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሁለተኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታውን በሀገር ውስጥ ማድረግ እንደሚችል ታውቋል።
የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒየን በመሆኑ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ለመሳተፍ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታውን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያው ዙር የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ የዩጋንዳውን ቪላ ከሜዳው ውጪ 2ለ1 አሸንፎ በመምጣት በሜዳው ያደረገውን ጨዋታ 1ለ1 ማጠናቀቁ እና በድምር ውጤት 3ለ2 አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር የሚያደርገውን የሁለተኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታውን ሀገር ውስጥ ማድረግ እንደሚችል ታውቋል።
የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ዛሬ የሁለተኛ ዙር የቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ስታዲየሞችን ሲዘረዝር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአዲስ አበባውን አበበ ቢቂላ ስታዲየም መጠቀም እንደሚችል ማረጋገጫ ተሰጥቶታል።