ከመቻል ጋር ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፈው አልዮንዜ ናፍያን ክሬኖቹን ለማገልገል ወደ ካምፓላ ያቀናል።
ጦሩ ለዋንጫ እንዲፎካከር ጉልህ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ዩጋንዳዊ ግብ ጠባቂ አልዮንዜ ናፍያን ሀገሩ ዩጋንዳን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ላይ እንዲወክል ጥሪ ደረሶታል። መቻል በፕሪምየር ሊጉ ያከናወናቸው ሙሉ ሰላሣ ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈው ይህ የሃያ ስምንት ዓመት ግብ ጠባቂ በ2022 በተካሄደው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሀገሩን ማልያ መልበስ የጀመረ ሲሆን ለሀገሩ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል። ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳንን በምታዋስነው እና በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክልል በምትገኘው የምዕራብ ናይል አውራጃ አድጁማኒ ከተማ የተወለደው ግዙፉ ግብ ጠባቂ ከዚህ ቀደም ከደቡብ ሱዳን እግር ኳስ ፌደሬሽን የቀረበለትን ጥሪ ውድቅ ካደረገ በኋላ በተደጋጋሚ ጊዜ ሀገሩን የመወከል ዕድል አግኝቷል።
አሰልጣኝ ፖል ፑት በቀጣይ ከደቡብ አፍሪካ እና ኮንጎ ለሚያደርጓቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቡና መጫወት የቻለው ግብ ጠባቂው ኢስማኢል ዋቴንጋ እና በሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተጫወተ በኋላ በቅርቡ ወደ ደቡብ አፍሪካው ክለብ ቬንዳ ያመራው ቻርለስ ሉክዋጎ በስብስባቸው ያካተቱ ቢሆንም አዲሱን የውድድር ዓመት ከሲዳማ ቡና ጋር ለማሳለፍ በዝግጅት ላይ የሚገኘው የባለፈው የውድድር ዓመት የዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ ወርቅ ጓንት አሸናፊው ቶም ኢካራን በስብስባቸው አላካተቱም።