የቀኝ መስመር ተከላካዩ ወደ ግብፅ ሊያቀና ነው

ከሁለት ቡድኖች ጋር የሊጉን ዋንጫ ከፍ ማድረግ የቻለው የመስመር ተከላካዩ ወደ ግብፅ ሊጓዝ ነው።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስድስት በስኬት የታጀቡ ዓመታትን ማሳለፍ የቻለው እና ከፈረሰኞቹ ጋር የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ በተለያዮ የሊጉ ክለቦች ሆነ በውጭ ክለቦች ሲፈለግ የቆየው ታታሪው የመስመር ተከላካይ ሄኖክ አዱኛ በመጨረሻም ማረፊያው የግብፁ ክለብ ሃራስ ኤል ሁዶድ ሆኗል።


በቀድሞ አጠራሩ ብሔራዊ ሊግ በሀላባ ከተማ ባሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ ድሬዳዋ ከተማን በመቀላቀል እራሱን በፕሪምየር ሊጉ ካስተዋወቀ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ካነሳበት ጅማ ከተማ ጋር ስኬታማ ቆይታ በማድረግ ከ2011 ጀምሮ ፈረሰኞቹን በመቀላቀል እስከ ተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በወጥ ብቃት ቡድኑን ማገልገል ችሏል።

የሄኖክ አዲሱ ክለብ ሃራስ ኤል ሁዶድ ከተመሰረተ 92 ዓመታት ያስቆጠረ ክለብ ሲሆን በታሪኩም ሁለት ጊዜ የግብፅ ዋንጫ አሸናፊ እንዲሁም አንድ ጊዜ የአሸናፊዎች አሸናፊ ሆኗል።

በ2010 እና በ2011 የውድድር ዘመን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ደደቢትን ከካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ያሰናበተው ቡድን ከአንድ የውድድር ዘመን በፊት ከግብፅ ሊግ በመውረድ ዘንድሮ ዳግም ወደ ሊጉ በመመለስ ተሳታፊ ሆኗል።

ሄኖክ ወደ ግብፅ በሚያቀናበት ሁኔታ ዙርያ የቪዛ ጉዳይ እና የጉዞ ሰነዶች እየተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣዮ ሳምንት ዝውውሩ ይፋ እንደሚደረግ ወኪሉ አዛርያስ ተስፋፂዮን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል ፤ ዛሬ ወደ ክለቡ ለማቅናት የተስማማው ሄኖክ አዱኛ ከጋቶች ፓኖም ቀጥሎ በክለቡ የተጫወተ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ሆኗል።