አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ከዋንጫው ጨዋታ በፊት ምን አሉ?

👉 “የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥያቄ በሌለው መልኩ የኢትዮጵያም ሆነ የምሥራቅ አፍሪካ ምርጡ ቡድን ነው።”

👉 “ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና አሰልጣኝ አሥራት አባተ በዕውቀትም ሆነ በልምድ አግዘውናል።”

👉 “ሌሎች ሀገራት ከመስተንግዷችን ብዙ መማር አለባቸው።”

👉 “ክለባችን ለሴቶች እግርኳስ እያደረገው ያለው ነገር አልተነገረለትም ፤ ለረጅም ዓመታት የዚህ ክለብ አሰልጣኝ ሆኜ በመሥራቴ ዕድለኛ ነኝ።”

👉 “ተጫዋቾቼ ዝግጁነታቸው ከሌላው ጊዜ የተሻለ ነው።”

የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከነሐሴ 11 ጀምሮ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን ነገ ሐሙስ ነሐሴ 23 ፍጻሜውን ያገኛል። ቀደም ብሎ በደረጃ ጨዋታ ሲምባ ኩዊንስ እና ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ 5፡00 ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን የፍጻሜው ጨዋታ 8፡00 ሲል በሀገራችን ተወካዩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ መካከል በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። እኛም ባለፉት ሦስት ዓመታት አንድ ጊዜ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ ሁለት ጊዜ ደግሞ ለዋንጫ ደርሰው በመለያ ምቶች በመሸነፋቸው  የኢንተርናሽናል ዋንጫ ረሃብ ላይ ከሚገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጋር ይህንን ቆይታ አድርገናል።

ስለ ውድድሩ አጠቃላይ ዕይታህ…

“ውድድሩ በጣም አሪፍ ነው። ያደረግናቸውን አራቱንም ጨዋታዎች አሸንፈናል። ውድድሩ ደግሞ በተለይ በእኛ ሀገር በመሆኑ ውድድሩን ለማስተናገድ ብዙ ሀገራት እንደሚሻሙ አውቃለሁ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም ወደዚህ ማምጣቱ የበለጠ አነቃቅቶናል ብዬ ነው የማስበው። ውድድሩ ላይ ደግሞ ብዙ ከባባድ ነገሮች አሉ አንደኛ ብዙ ክለቦች ከግማሽ በላይ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ነው ያላቸው ፤ እኛ ሀገር ሦስት ነበር ዘንድሮ ነው አምሥት የሆነው እነሱ ጋር ግን ሕግ ያለም አይመስለኝም ለምሳሌ ሲምባን ብናይ ከ7 በላይ ኬንያውያን ተጫዋቾች ነው ያሉት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ውድድሩ በጣም እየከበደ መምጣቱን ነው ያየነው እና ክረምት እንደመሆኑም ዝናብ አለ ልምምድ ታቋርጣለህ ፤ ጨዋታ ላይም ጭቃ ይሆናል። እነዚህን ፈታኝ ጊዜዎች አሳልፈናል እና በአጠቃላይ ይህንን መልክ ይዞ ለእኛ ለአሰልጣኞችም ሆነ ለተጫዋቾችም ፈታኝ ሆኖ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብዬ አስባለሁ።”

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለፉት ሦስት ዓመታት በምን ተሻሽሎ ቀረበ?

“የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥያቄ በሌለው መልኩ የኢትዮጵያም ሆነ የምሥራቅ አፍሪካ ምርጡ ቡድን ነው። ምናልባት ዋንጫ አልበላንም እንጂ ዋንጫ የበሉት ራሱ ተደጋጋሚ መድረኩ ላይ ሲታዩ ዐላየንም። ዓምና ዋንጫ ያነሳው JKT QUEENS የለም በሱ ሲምባ ነው የመጣው። ሀገሩ ላይ ሲዘጋጅ በልቶ የነበረው VIHIGA QUEENS የለም ኬንያ ፖሊስ ነው የመጣው ሲምባም ከዋንጫው ወጥቷል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግን በአራቱም ውድድሮች ግማሽ ፍጻሜ ደርሶ እንደገና ደግሞ ሁለት ጊዜ ለዋንጫ ደርሶ አጥቷል። በዚህ ዓመት ግን ይሳካልናል ብለን ነው የምናስበው እና ይህንን ጥንካሬውን ማየት አለብን። ሌላው መታወቅ ያለበት ሰዎች እንዲረዱት ዓምና ስምንት ተጫዋቾች ስማቸውን መጥራት ይቻላል ፤ አራቱ ከኋላ ያሉ ተጫዋቾች እነ ብዙዓየሁ ታደሰ እነ ትዝታ ኃይለሚካኤል ፣ ብርቄ አማረ ፣ እፀገነት ብዙነህ ፤ ንቦኝ የን እና አርያት ኦዶንግ ደግሞ ወደ ታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ አቅንተዋል እና መዲና ዐወልም ጉዳት ላይ ነው ያለችው ፤ ሀገራችን ላይ በጥንካሬዋ የምትታወቀው አጥቂዋን ሎዛ አበራን ያጣ ቡድን ነው። እነዛን ተጫዋቾች አጥቶ ሀገር ላይ ውጤታማ ሆኖ እንደገና በዚህ ውድድር ላይ ደግሞ እነ ንግሥት እና ሴናፍን ይዘን እንዲሁም ከኋላ እነ ቅድስትን ይዘን በሀገር በቀል ተጫዋቾች አሁንም ለዋንጫ መቅረባችን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ላይ እየሠራ ያለውን ነገር የሚያሳይ ነው። እንዲህም ሆኖ ግን እንደ ዋንጫ ያልተሳካልን ነገር አለ ፤ ባለቀ ደቂቃ እየገባብን ፣ በተለይ የኬንያው 94ኛ ደቂቃ ላይ ነው ፔናሊቲ ተሰጥቶብን ጎል የገባብን ፤ ባለፈውም የተቻለንን ሁሉ ጥረን ምንም ማድረግ አይቻልም ሁለት 120 ደቂቃ ተጫውተን በጥሎ ማለፍ በፔናሊቲ አጣነው እና በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካም ደረጃ ሦስት ጊዜ የቀረበ የለም። ከጥንካሬያችን አንጻር እነሱም ዋንጫ ቢያነሱ ብለው ይመኙልናል እና በተለየ መልኩ እንግዲህ ያቺን ያጣናትን ጊዜ ለማካካስ ከተጫዋቾቼ ጋር ምርጥ ስነልቦና ላይ ነው ያለነው። በስነልቦና ደረጃ የካፍ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ የቪዲዮ አናሊሲስ ልኮልኝ እሱን በደንብ ወስደናል ፤ ቀጥሎ ደግሞ አሰልጣኝ አሥራት አባተም የሴቶች እግርኳስ ላይ የቆየ ስለሆነ ልምዱን ሰጥቷል። ተጫዋቾቼ ዝግጁነታቸው ከሌላው ጊዜ የተሻለ ነው።”

ከሌሎች ክለቦች ምን ተማራችሁ?

“እንድ ሲምባ ዓይነት ቡድን በሁሉ የተራጀ ነው። ከሕክምና እና ከአሰልጣኝ ቡድናቸው ጀምሮ ያላቸው ዲሲፕሊን እና ሌሎች ነገሮች በሙሉ ልንማርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። አጠቃላይ ተጫዋቾች የሚያሳይዋቸው ነገሮች ከምሥራቅ አፍሪካ አልፎ በአውሮፓ ደረጃ ነው የምገምታቸው። ሌላው ኬንያ ፖሊስ ከምድብ በጭንቅ አልፎ ሲምባን ያሸነፈበት እግርኳስን መገመት እንደማይቻል ያሳያል ለምሳሌ በሁለት ጎል ብቻ ነው የደቡብ ሱዳኑን የይ ጆይንት ስታርስ የበለጠው አራት ነጥብ ይዞ ግን በጣም ግዙፉን ቡድን አሸነፈ። ሀገራችን ላይ ደግሞ እግርኳስን ለሌላው ቢያስተምሩ ፣ ቢነግሯቸው እላለሁ ለምሳሌ እኔ ልምድ አለኝ አራተኛ ጊዜዬ ነው በመድረኩ የዘንድሮው እዚህ ነው ሌሎቹ ውጪ ነበሩ። እዛ ስንሄድ ያንገላቱናል። በተለይ በታንዛኒያ ከሁለት ክለብ ጋር ሆቴል አስይዘው ገበያ መሃል ያደርጉሃል ኡጋንዳ ላይ እኛ እና የብሩንዲውን ክለብ አንድ ላይ ነው ያደረጉን ፣ ምግብ የሚባል ነገር የለም ሽሚያ ነው ፤ ሁለት ምግብ ብቻ ነው የምትበላው በደንብ ነው የሚያንገላቱን ግን ልክ እንደ ኢትዮጵያ ቢሆን ፤ ኢትዮጵያ እኮ አንዳንድ ሆቴል ሰጥታ ነው። እኛ እኮ በባሕላዊ መንገድ እንግዶችን ተቀብለን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ነው አቀባበል የሚያደርገው። እዛ እኮ ጭራሽ መቀበል የሚባል ነገር የለም ጭራሽ አንድ ሁለት ሰው ብቻ ነው የሚመጣው። እኛ ብቻ ከእነሱ የምንማር ሳይሆን እነሱም ከእኛ ይማሩ በዝግጅታችን። በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደስተኛ አልነበረም እዛ ሄደን ካፍ ሁሉን ነገር ይችላል ብለን ሄደን ተጨማሪ ክለቡ ነው ወጪ እያወጣ ለተጫዋቾቻችን ተጨማሪ ምግብ እየገዛን ያቆየን እና ጠግቦ መብላት በራሱ የሚከብድበት ነው እዚህ ግን ለየብቻቸው ነው ባለ ሦስት ፣ አራት ፣ አምስት ኮከብ ሆቴል የሚይዙት እና ከእኛ መማር አለባቸው። እንደ ሲምባ እና ኬንያ ፖሊስ ዓይነት ጠንካራ ክለብ ቢኖርም የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ለሁሉም የምሥራቅ አፍሪካ ክለቦች ምሳሌ መሆን አለበት። በነገራችን ላይ ደመወዝ ክፍያ የለውም አበል ብቻ ነው ያለው። ሦስት ክለብ አለው የትምህርት ቤት ክለብ ነው ፕሮፌሽናል ምንም የለም። ትውልድ ላይ ነው የሚሠሩት በየትኛውም የአፍሪካ ውድድር አናውቃቸውም ግን ተዓምር የሚሠሩ ተጫዋቾች ናቸው። ያለ ድጋፍ እዚህ የደረሱ ናቸው እና በትንሽ ነገር ቡድን መሥራት እንደሚቻል ካዌምፔ ሙስሊም ዐሳይቶናል። ይሄንን ከእነሱ ወስጃለሁ ብዬ አስባለሁ።

ስለ ቡድናችሁ ከተጠየቁ አሰልጣኞች መካከል የኬንያ ፖሊስ ምክትል አሰልጣኝ “ታክቲካሊ ጠንካራ ናቸው” ብሎ ነበር በአንጻሩ የካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ አሰልጣኙ “ታክቲካሊ ይቀራቸዋል” ብሏል አንተ በየትኛው ትስማማለህ?

“እኔ በኬንያ ፖሊሱ አሰልጣኝ ሀሳብ ነው የምስማማው። ኬንያዎች ከዚህ በፊትም ለዋንጫ ባለፍንበት ጊዜ በታክቲክም በቴክኒክም ከእኛ የተሻሉ ናቸው። “ኢትዮጵያ ናት ያደገችው ወይንስ ንግድ ባንክ ብቻ ነው እንደዚህ ያደገ? የኢትዮጵያን ቡድን በዚህ ደረጃ ዐይቼ አላውቅም” ብሎ ነው የተናገረ ዓምና የVIHIGA QUEENS አሰልጣኝ። ግን ይሄኛው የካዌምፔው አሰልጣኝ በምን እንደተናገረ አላውቅም። መሳይ ባስቆጠረችው ጎል የሱን ታክቲክ እንዴት እንዳፈረስንበት እና እሱ አሳስሮት የነበረውን እንዴት እንደፈታነው ታይቷል። ይሄ የእኛን ቲም ለማውረድ የተጠቀመበት ነው ስላልተሳካለት ነው ብዬ ነው የማስበው እና ምናልባት እንደዚህ ዓይነት አሰልጣኞች ተሸንፈው እንደዚህ ሲናገሩ ሙያቸውንም እጠራጠራለሁ ምክንያቱም ይሄ የሙያ እና የዕውቀት ጉዳይ ስለሆነ የእኛ ቡድን 45ኛ ደቂቃ ላይ ነው ጎል ያገባው አንዱ ታክቲክ ይሄ ነው ብዙ ቦታ አሳስሮብን ተሳክቶለታል በዚህ አጋጣሚ አድናቆቴን ሳልሰጥ አላልፍም ቅድምም ስለ ክለቡ ስትራክቸር በደንብ ተናግሬያለሁ ሙያ ስለሆነ ነው የተናገርኩት። ሁለተኛ ደግሞ ባለቀ ሰዓት ተቆጥሮበታል ስለዚህ ሁለቱንም 45 ደቂቃዎች አልቻላቸውም እና እነዛን ነገሮች ባለመቻልህ “ይቀራቸዋል” ብለህ ክፍተት መናገር በእኔ በኩል ተቀባይነት የለውም። ተጫዋቾቼ ግን እስካሁን ድረስ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ያላቸውን ሁሉ በማድረግ ጠንካራ ናቸው እና ይሄንን የአሰልጣኙን ንግግር አልቀበለውም።”

በቡድንህ አባላትም ሆነ በክለቡ አመራሮች ለዋንጫው ያለው ዝግጁነት ምን ያህል ነው?

“ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ አንድ ደስ የሚል ነገር አለ። የክለቡ የበላይ ጠባቂ የሚመራው ቦርዱን ነው ፣ ቦርዱ ደግሞ የሚመራው ማኔጅመንትን ነው ፣ ማኔጅመንት ደግም የሚመራው እኛን አሰልጣኞችን ነው ፣ እኛ ደግሞ ተጫዋቾቻችንን እንመራለን። ይሄ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት የለም። የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆኖ ዋንጫ የምንበላ ከሆነ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዝግጅት ወደኋላ አይልም ያ ይታወቃል። አልነገሩንም ነገር ግን ሳልጠራጠር የማወራው ነገር ነው። ሁሉም ነገሮች በስፖርታዊ ምግባሮች ስለሚመሩ ዛሬ ይሄን አደርግልሃለው ይሄን አደርግልሃለው ቢባል ተጫዋቾችም ሜዳ ላይ መሥራት ስለሚያቅታቸው ሥራቸውን ከሠሩ በኋላ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ለወንዶች የተደረገው ነገር ነው አዳማ ላይ የተደረገልን አሁን ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ ስለሚሆን ዐይተናቸው የማናውቃቸው ነገሮች እንደሚደረጉ ተስፋ እናደርጋለን ግን በእኛ በኩል የቤት ሥራዎቻችንን ሠርተን በክለባችን እንተማመናለን እና ክለባችን ለሴቶች እግርኳስ እያደረገው ያለው ነገር አልተነገረለትም። ከወንዶች እኩል ደመወዝ ይከፈላቸው ፣ ከወንዶች እኩል ሆቴል ይቀመጡ ፣ ከወንዶች እኩል የማቴሪያል ዝግጅት ይደረግላቸው የሚል በአጭር ጊዜ የሴቶችን ተሳትፎ ያወጀ ክለብ ነው እና በዚህ አጋጣሚ ለረጅም ዓመታት የዚህ ክለብ አሰልጣኝ ሆኜ በመሥራቴ ዕድለኛ ነኝ።”

በምድብ የመጨረሻ ጨዋታ ካሸነፋችሁት ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ ጋር ነው የፍጻሜ ጨዋታችሁ ምን ዓይነት ጥሩ ጎን አለው?

“የባለፈው ማሸነፍ ለዛሬ ዋስትና አለው ብዬ አላምንም ምክንያቱም ሌላ 90 ደቂቃ መፋለም አለብን። ግን በስነልቦና ይጠቅመናል ፤ ጎል ቀድመን የምናገባባቸው ከሆነ እነሱም ባለፈው የነበረባቸውን ነገር ማሰባቸው አይቀርም እግርኳስ ስለሆነ ማለት ነው። ነገ ሌላ መልክ ነው። ባለፈው ከምድብ ለማለፍ ነበር ለጥቂት ነው የተረፉት እና የተለየ ነገር ይዘው ይመጣሉ ብዬ አላስብም እኛ ግን ባለፈው ከነበረን የተሻለ ነገር ይዘን እንመጣለን። እግረመንገዴን ማንሳት የምፈልገው ምንድንነው እኛ በአካል ፣ በአዕምሮ ፣ በመንፈስ ተዘጋጅተናል። በቴክኒክም በታክቲክም በሳይኮሎጂም ተጫዋቾቼ ተዘጋጅተውበታል ግን ከታዘብኩት አኳያ ሀዋሳም ሆነ አዳማ እያለን ብዙ ሕዝብ ነበር የሴቶችን እግርኳስ የሚያየው ኬንያ ዋንጫውን ያስቀረብን ስታዲየም ሞልቶ ጠብቆን ነበር ለምን ለሀገራቸው ክለብ እጅግ ከመጠን በላይ ድጋፍ ነበረ በዛ ተደግፈውም ዋንጫውን በልተውታል። ታንዛኒያ ላይ ሲምባ ሲበላ አዛም ስታዲየም ላይ ብዙ ሕዝብ ነበር እንደገና ደግሞ ዩጋንዳ ላይም ሙሉ ስታዲየም ነበር የሞላው ያ ደግሞ 12ኛ ተጫዋች ነው ብዬ ነው የማስበው እና አንድ መረሳት የሌለበት ነገር ምንድን ነው ኢትዮጵያ ለሴቶች እግርኳስ ዕውቅና ከሰጠች ወይም ደግሞ ብሔራዊ ቡድን የተመሠረተ እ.ኤ.አ 2004 ላይ ነበር። በዚህ በ22 እና በ23 ዓመት ምንም ዓይነት የሴት ውድድር አላስተናገደችም የታዳጊ ውድድሮችም ቢሆን። ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው። ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅታ ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በላን ብለን እናወራለን እንደ ታሪክም ተመዝግቧል ካልበሉት እንሻላለን። ከዚህ በኋላ ዋንጫ ለመብላት ብቸኛው መንገድ ይሄ ነው። ብቸኛው አማራጭ ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይደግፈናል ፣ ጥቂት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደጋፊ አለ ሌሎች ግን አልበዛንም። በጣም ቀዝቅዟል። ውድድሩ እንደ ኮቪድ ባለ ምክንያት ወደ ክልል ሄዶ ከአራት ዓመታት በኋላ ነው አዲስ አበባ ተመልሼ ውድድር ያደረግኩት። እግርኳስ አፍቃሪያን ነገ የእናንተ ልጆች የሚጫወቱበት ስለሆነ እባካችሁ ድጋፍ ስጡን ተቀዛቅዟል። ከዚህ በላይ ብትደግፉን ለተጫዋቾች ሞራል ይኖራል እና ተጋጣሚንም በስነልቦና እናዳክማለን።”

በመጨረሻ ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ በተለይም ለሚዲያው…

“ያለፈው ጨዋታ እንዳለቀ እጅግ ብዙ ጋዜጠኞች ነበር የተገኙ በዚህ አጋጣሚ ደስ ብሎኛል። ሚዲያ እና እግርኳስ አንድ ናቸው ፤ እግርኳስ ያለ ሚዲያ ባዶ ነው ሚዲያም ያለ ስፖርት ባዶ ነው። እንግሊዝን እንደዚህ ያገነናት ሚዲያ ስለሆነ ማለት ነው። ከምሥራቅ አፍሪካ ሚዲያዎች ደግሞ የኬንያ ሚዲያ እንደ እንግሊዝ ነው የሚሆንብህ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚዲያ ኢንደስትሪ በጣም በዝቷል እና ሶሻል ሚዲያን ጨምሮ አጠቃላይ ሚዲያ የተባለ በሙሉ ይህንን ሀገሩን የሚወክለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስለሚጫወት ጥሪያቸውን እንዲያቀርቡ እና በርካታ ሕዝብ እንዲመጣ ማለት ነው። የአምስት ሰዓቱ የሲምባ እና የካዌምፔ ሙስሊም ጨዋታም ቢሆን በጣም ጠንካራ ጨዋታ ነው እና ከእሱ ጀምሮ የራሳቸውን ክለብ ለዋንጫ እንዲደግፉ ብለው ጥሪያቸውን ቢያስተላልፉ እላለሁ።”