የሴካፋ ተሳታፊው ክለብ ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጋር ለመሥራት ቅድመ ውይይት አደረገ።
በሴካፋ የሴቶች ውድድር ተሳታፊ የሆነው የሩዋንዳው ራዮን የሴቶች ክለብ በምድብ አንድ ተደልድሎ ከምድቡ ማለፍ ሳይችል ቀርቶ ዛሬ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። በምድብ የመጀመሪያ ጨዋታው ከሀገራችን ተሳታፊ ክለብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተገናኝቶ በጥሩ ፉክክር ሶስት ለሁለት በሆነ ውጤት ተረቷል። በባንክ በተረቱበት ጨዋታ ጎሎችን በማስቆጠርም ሆነ በእንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩትን ተጫዋቾች መነሻ የሆነውን የምልመላ ማዕከል ሲያጣራ የቆየው ራየን እነ ሴናፍ ዋቁማ፣ አረጋሽ ካልሳ እና መሰል ተጫዋቾችን ያበረከተውን የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጉብኝት አድርገዋል።በአካዳሚው የተገኙት የቡድኑ ተጫዋቾች፣ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት እና የክለብ አመራሮች የፕሮጀክቱ ትልቅነት እንዳስገረማቸው የገለፁ ሲሆን በስተመጨረሻም ከአካዳሚው አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በቀጣይ በተጫዋች ምልመላ፣ በወዳጅነት ጨዋታ እና የልምድ ልውውጥ ላይ ለመስራት ንግግር የተደረገ ሲሆን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ለመፈራረምም ቀጠሮ ተይዟል። የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበስ እንየው ከሩዋንዳ ኢምባሲና ከፌዴሬሽኑ ሰዎች ጋር ለሚደረግ ውይይት ዝግጁነታቸውን ገልጸው ግንኙነቱ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል። የራዮን ስፖርት ክለብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናሚኒ ፓትሪክ በበኩሉ ባያቸው ነገሮች መደሰቱን ገልጾ በአርማ ልውውጥ የዕለቱ መርሐግብር ተቋጭቷል።