በነገው ዕለት በካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ የፍፃሜ ጨዋታውን በምድብ ተገናኝቶ ከነበረው የኬኒያ ፓሊስ ቡሌትስ ጋር የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከነገው ወሳኝ ጨዋታው በፊት የዝግጅት ክፍላችን ከተከላካይ አማካዩዋ ጋር ቆይታን አድርጓል።
እግር ኳስን የጀመረችው በትውልድ ቦታዋ አርባምንጭ ከተማ ክለብ ውስጥ ነው። በጊዜ ሂደት በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ውስጥ በተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ እጅግ ተደናቂ በመሆን በመቻል እንዲሁም ላለፉት አራት ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መለያ እየተጫወተች ትገኛለች። በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ከክለቧ ጋር ደግሞ በሴካፋ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ መድረክ ላይ በልዩነት ከሚታዩትም መካከል መሆኗን አስመስክራለች።
በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን እያሰናዳች በምትገኘው የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምድብ እና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን በድል እየተወጣ ለፍፃሜ ሲደርስ በተለይ የተከላካይ አማካዩዋ የዩጋንዳውን ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስን በጥሎ ማለፍ አሸንፎ ለፍፃሜ ሲቀርብ ከርቀት ያስቆጠረቻት ማራኪ ሁለተኛ ጎል ቡድኑን በነገው ዕለት ከኬኒያ ፓሊስ ቡሌትስ ጋር ለዋንጫ ትንቅንቅ እንዲበቃ አድርጋለች። ከነገው የፍፃሜ ጨዋታ በፊትም ከላይ ዘርዘር ካደረግንላችሁ የንግድ ባንክ የመሐል ሜዳ ተጫዋቿ እመቤት አዲሱ ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርገናል።
ስለ ምድብ ጨዋታዎች እና ከካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጋር ስለነበረው ጨዋታ…
“በምድብ ጨዋታው ከመጀመሪያው ጀምሮ ነጥቦችን መያዛችን አሪፍ ሆኖ ሳለ የነበረን ጥንካሬም አለ የነበሩብን ድክመቶችም ነበሩ ያንን ደግሞ እንደ ቡድን ሠርተን የተሻለ ነገር እየሠራን አሁን ፋይናል ላይ ደርሰናል።”
በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ወቅት ቡድኑን አሸናፊ ያደረገ ግብ ማስቆጠሯ እና ስለፈጠረባት ስሜት…
“ጎሉ ለእኔ በሕይወቴ የመጀመሪያው ነው ብዬ ነው የማስበው ነገር ግን ወደ ጎል በምመታበት ሰዓት ወደ ጎል እንደምመታ እርግጠኛ ነበርኩ እና ኳሱ ሲመጣ ጎሉ ላይ ለመምታት ወስኜ ነበር የመታውት ኳሱም ሄዶ ተቆጥሯል። በእኔ ጎል ውጤቱ መሆኑ በጣም ደስተኛ ነኝ የእኔንም የቡድን አጋሮቼንም ደስታ በጎሏ ውስጥ ስላየሁ በጣም ደስተኛ ነኝ እኔም ደስ ብሎኛል።”
ቡድኑ ከዚህ በፊት በውድድሩ ላይ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ደርሶ ሳያሳካ ስለ ቀረው ዋንጫ እና ዘንድሮ በሀገራችን ውድድሩ በመዘጋጀቱ ያለፈው ስህተት ሳይደገም ይህንን ዋንጫ እንዲያገኝ ምን መደረግ አለበት ብለሽ ታስቢያለሽ?
“አሁን የምንጫወተው በህዝባችን እና በደጋፊያችን ፊት ነው። ለየት የሚያደርገው ካለፉት ከሦስት ውድድሮች ይሄ ሀገራችን ላይ መሆኑ ይሄ ለእኛ ለየት ያለ ነገር ነው ፣ ደጋፊያችንም አስራ ሁለተኛ ተጫዋች ነው እና ህዝቡ መጥቶ ቢደግፈን እጅግ በጣም የተሻለ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የነበሩ ቡድኖች ቻምፒዮን ሲሆኑ ይሄንን ነገር እየተጠቀሙ ነበር። ይሄም አድቫንቴጅ ነው ሌላው ግን ከነበሩብን ስህተቶች እየተማርን ነው የመጣነው ብዬ አስባለሁ ፣ አሁን ሀገራችን ላይ መሆኑ በይበልጥ ኮንፊደንስ እንዲሰማን ያደርጋል ብዬ አስባለሁ ፤ በደጋፊ ፊት ስለሆነ ያ ነገር አድቫንቴጅም አለው።”
በምድብ ጨዋታ አሸንፋችሁት ከነበረው ኬኒያ ፓሊስ ቡሌትስ ጋር ነው በፍፃሜ የተገናኛችሁት የቡድናችሁ አሁናዊ ስሜት ምን ይመስላል ተነሳሽነታችሁስ?
“ያለን የመጨረሻ ጨዋታ ነው። ሁላችንም በጋራ እየተነጋገርን ነው ያለነው እንደ ቡድን እንደ አሰልጣኝም የሚሰጡን ነገር አለ ይሄ ደግሞ በጋራ እንድናስብ ያደርገናል ብዬ አስባለሁ። እስከ ዛሬም የመጣነው በጋራ ነው እና አንድ ላይ በጣም ጥብቅ የሆነ ነገር እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ። የመጨረሻ ጨዋታ ነው ፋይናል ደግሞ ምሕረት የለውም ስለዚህ ያለንን ነገር አውጥተን ከፈጣሪ ጋር እናደርገዋለን ብዬ ነው የማስበው።”