በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በመካሄድ ላይ ያለው
የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ
ነገ የኢትዮጵያው ተወካይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ በሚያከናውኑት የዋንጫ ጨዋታ ፍፃሜውን ያገኛል። እኛም የኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ ዋና አሰልጣኝ ቤልዲን ኦደምባ ከተጠባቂው ጨዋታ በፊት ከሴካፋ የሚድያ ክፍል ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።
ስለ ቡድናቸው ዝግጅት ?
“የመጨረሻውን ልምምድ አገባደን ለጨዋታው ተዘጋጅተናል።”
ቡድናቸው በውድድሩ ስላጎለበተው ነገር ?
“በጥሩ ሁኔታ እየተከላከልን ነው ፤ ለዚህም ማሳያው ባለፉት ጨዋታዎች ጎል እየተቆጠረብን አይደለም።”
ከንግድ ባንክ ጋር በድጋሚ ስለመጫወታቸውና ዋንጫውን ለማንሳት ቁልፉ ነገር ብለው ስለሚያስቡት ጉዳይ?
“ቁልፉ ነገር ጥንካሬያቸውን በደንብ አይተናል በልምምድ ሜዳ ላይም በሚገባ ሰርተንበታል ፤ ከዚህ በተጨማሪም የተጋጣሚያችን ድክመቶቹም የት እንዳሉ ተምረናል ያንንም እንጠቀምበታለን።”
በግማሽ ፍፃሜው ስለተጠቀሙባቸው ተጫዋቾች
“በግማሽ ፍፃሜው ጨዋታ ላይ አቀራረባችን እንደገና ማየት ነበረብን ፤ እንደማስበው ማስተካከያው በትክክል ሰርቷል ብዬ አምናለሁ። አሁንም ለውጥ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ጥሩ ለውጦችን ማድረጋችን እንቀጥላለን። በተጫዋቾቻችን በተለይም በአዳዲሶቹ ማመን አለብን፤ አንድ ነገር ሊያሳዩን ይችላሉ። በነገው ጨዋታ ጥሩ ነገር እንደሚሰጡንም እናምናለን።”
በመጀመርያው ውድድሯ ወደ ፍፃሜ ማለፏ ስለ ፈጠረላት ስሜት ?
“ገና ወደ ውድድሩ ከመምጣታችን በፊት እስከ ፍፃሜ ልንደርስ እንደምችል ተስፋ አድርገን ነበር የመጣነው። ነገርግን ቀላል እንደማይሆን ገምተን ነበር። በተለይም የምድብ ጨዋታዎች ከባድ ነበሩ፤ ትንሽ ተቸግረናል። ነገር ግን በስነ ልቦናው ረገድ በሂደት ወደ ጥሩ ነገር በመምጣታችን እና ወደ ፍፃሜው ጨዋታ በመድረሳችን ደስተኛ ነኝ።”
ከቡድኑ መሻሻል በስተጀርባ ስላለው ሚስጥር ?
“አሁንም እየሰራን ነው ነገም ጥሩ ነገር ይዘን እንደምንወጣ ተስፋ አደርጋለሁ።”
በውድድሩ በወንድ አሰልጣኞች መካከል ያለች ሴት አሰልጣኝ መሆኗ ስለፈጠረባት ስሜት?
“ብዙ ጊዜ ሴት አሰልጣኝ መሆኔን እረሳዋለሁ።
ወደ ሜዳ ከገባሁ አሰልጣኝ ብቻ እንደሆንኩ ነው የማስበው።”