ያለፉትን ዓመታት ከነብሮቹ ጋር ቆይታ የነበረው አጥቂ ወደ ቢጫዎቹ ለማምራት ከጫፍ ደርሷል።
በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመሩ በቢሾፍቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸው በማድረግ ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሀድያ ሆሳዕና ቆይታ ያደረገውን ዳዋ ሆቴሳን ለማስፈረም ከስምምነት ደረሱ።
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በ1761 ደቂቃዎች ነብሮቹን ያገለገለው ይህ ተጫዋች በአዲሱ የውድድር ዘመን ወልዋሎ ዓ/ዩ ለመቀላቀል ከቡድኑ አመራሮች ጋር ያካሄደው ድርድር በስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ ባለፈው ሳምንት ዓርብ የህክምና ምርመራውን ያጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይ ቀናት ፊርማውን እንደሚያኖር ይጠበቃል።
እግር ኳስን በክለብ ደረጃ በናሽናል ሲሚንቶ ከጀመረ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከዚያ ቀጥሎም በሁለት አጋጣሚዎች አዳማ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች እና በዋናው ቡድን ደረጃ ማገልገል የቻለ ሲሆን ተጫዋቹ ከቀድሞ አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለ ጋር በድጋሚ የሚገናኝ ይሆናል።
ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ወደ ወልዋሎ ለመቀላቀል ከተስማማ በኋላ በመሀል ወደ ጋናው ክለብ ኸርትስ ኦፍ ኦክ ለማቅናት ተቃርቦ የነበረው ጋናዊው አማካይ ራዛቅ ቃሲም በስተመጨረሻ ወደ ወልዋሎ ለመፈረም ከስምምነት ደርሶ ቡድኑን ተቀላቅሏል።