በባቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየሰሩ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማካተት ተስማምተዋል።አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ እና ተጨማሪ ሁለት አዳዲስ ረዳቶችን በመቅጠር በባቱ ከተማ ለ2017ቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየከወኑ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች ቀደም ብለው በዝውውሩ ስንታየሁ መንግሥቱ ፣ አቡበከር ወንድሙ ፣ አሜ መሐመድ ፣ ዳግም ተፈራ እና ዳንኤል ተሾመን የስብሰባቸው አካል ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን አሁን ደግሞ ተጨማሪ አራት ተጫዋቾችን በማካተት የአዳዲስ ተጫዋቾችን ቁጥር ዘጠኝ ለማድረስ ተቃርበዋል።
ኃይለሚካኤል አደፍርስ የአዳማ አዲሱ ተጫዋች ሆኗል። የቀድሞው የሰበታ ከተማ የግራ መስመር ተከላካይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሁለት የውድድር ዘመናትን አሳልፎ ወደ አዳማ ከተማ አምርቷል።
ዳንኤል ደምሱም ወደ ቀደመ ክለቡ ተመልሷል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ሕይወቱን ከጀመረ በኋላ በባህር ዳር ከተማ ፣ በወልዲያ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ መቐለ 70 እንደርታ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና የተጠናቀቀውን ዓመት በወልቂጤ ከተማ ያሳለፈው የተከላካይ አማካዩ በድጋሚ ከዚህ ቀደም ወደተጫወተበት አዳማ ከተማ የሚመልሰውን ዝውውር ለማገባደድ ተስማምቷል።አማካዩ ሙሴ ካቤላም ወደ አዳማ ያመራ ተጫዋች ነው። ተጫዋቹ በአማካይ ስፍራ ላይ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ጅማ አባጅፋር ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ያለፈውን ዓመት ደግሞ በኢትዮጵያ መድን ቆይታ ነበረው።
አራተኛው ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው ስዩም ደስታ ነው። በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን በማድረግ የሚታወቀው ከአርባምንጭ የተገኘው እና በአጥቂነት ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ፣ ይርጋጨፌ ቡና እና በ2016 ደግሞ በስልጤ ወራቤ ያሳለፈው አጥቂ መዳረሻው አዳማ ሆኗል።