ንግድ ባንክ የካፍ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ቻምፒዮን ሆኗል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመዲናችን በተዘጋጀው የካፍ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣርያ ውድድር የዋንጫ ጨዋታ የኬኒያ ፓሊስ ቡሌትስን 1ለ0 በመርታት እና አሸናፊ በመሆን በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ምስራቅ አፍሪካን መወከላቸውን አረጋግጠዋል።

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ መድረክ ላይ ምስራቅ አፍሪካን የሚወክለውን ክለብ የሚለየው የፍፃሜ ጨዋታ በዩጋንዳዊቷ የ32 ዓመት ዓመት ዳኛ ሻሚራህ ናቫዳ መሪነት የተጀመረ ነበር። በጥሎ ማለፉ ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስን አሸንፈው የነበሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ምንም የአሰላለፍ ለውጥን ሳያደርጉ ባደረጉት በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስር ያህል ደቂቃዎች ኬኒያ ፓሊስ ቡሌቶች በሽግግር የጨዋታ መንገድ በተሻለ ጥቃት ለመሰንዘር የጣሩበት ሆኖ ታይቷል። በፈጣን መልሶ ማጥቃት ከጅምሩ ፑሪቲ አንየቱ አከታትላ ባደረገቻቸው ሙከራዎች እና ታሪኳ በርገና ባመከነቻቸው ሁለት አጋጣሚዎችን ፈጥረው ተስተውሏል።

ከራስ ሜዳ የሚደረጉ የአንድ ሁለት ቅብብሎችን ተጠቅመው ሜዳውን በመለጠጥ በመስመር ማጥቃት የመረጡት ንግድ ባንኮች ከቆሙ ኳሶች ሁለት ዕድሎችን ሲፈጥሩ በ15ኛው ደቂቃ በግራ በኩል አረጋሽ ከቅጣት ምት ወደ ግብ መታ የግብ ዘቧ አንዱ ኩንዱ ኩዋማሲ ስትመልሰው በተመሳሳይ ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ሴናፍ ዋቁማ ላይ ሊዲያ ዋጋንዳ የሰራችባትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን ቅጣት ምት መሳይ ተመስገን መታ አሁንም ግብ ጠባቂያዋ አድናባታለች። ጨዋታው ቀጥሎ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች እምብዛም ወጥ ያልሆኑ ቅብብሎችን ሲያስመለክተን ወደ ግራ አድልታ በይበልጥ በጥልቀት መጫወትን የመረጠችውን የንግስት በቀለን እንቅስቃሴ ንግድ ባንኮች ለመጠቀም ሲዳዱ በተሻለ ማጥቃቱ ላይ የተዋጣላቸው ነበሩ።

በዚሁ የጨዋታ መንገድ 23ኛው ደቂቃ ላይ ንግስት ያገኘችውን ኳስ በጥሩ ዕይታ ለሴናፍ ሰጥታት አጥቂዋ ያገኘችውን ኳስ ብትሞክርም የግቡ ቋሚ ብረት መረቡ ጋር ሳይደርስ አግዶታል። የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች አንድ ነገር ለመፍጠር ፈጠን ብለው ቅብብሎችን የሚጠቀሙት ንግድ ባንኮች በንግሥት እና አረጋሽ አማካኝነት መልካም አጋጣሚን ፈጥረው ወደ ጎልነት መለወጥ ሳይችሉ ቀርተዋል በተለይ ንግስት ግብ አስቆጥራ ከጨዋታ ውጪ ከተባለ በኋላ አጋማሹ ተጋምሷል።


ከዕረፍት መልስ በይበልጥ ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተሻለ የማጥቃት ተሳትፎ ነበራቸው። አረጋሽ ከርቀት ባደረገቻት ሙከራ የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል መፈተሽ የቻሉት ንግድ ባንኮች በሁለት አጋጣሚዎች በአረጋሽ እና ታሪኳ አማካኝነት ከቅጣት ምት ሙከራን ያደረገው ቡድኑ በተመሳሳይ በግብ ጠባቂያዋ አንዱ ኩንዶ ተመልሶባቸዋል። መሐል ሜዳውን ከመስመር ተጫዋቾች ጋር በማጣመር ጨዋታውን በአግባቡ እየተቆጣጠሩ የቀጠሉት ንግድ ባንኮች በ60ኛው ደቂቃ አረጋሽ ካልሳ ከቀኝ በጥልቅ ይዛ ገብታ ከሳጥን ጠርዝ መትታ ግብ ጠባቂዋ አንዱ በጥሩ ቅልጥፍና መልሳባታለች።

ወደ ጨዋታ ለመግባት በእጅጉ ከብዷቸው ይታዩ የነበሩት ኬኒያ ፓሊስ ቡሌቶች 75ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ኔሊ ሳዌ አደገኛ ሙከራን አድርጋ ታሪኳ በርገና እንደምንም አውጥታባታለች። የጨዋታውን አስራ አምስት የመጨረሻ ደቂቃዎችን ግብ አስቆጥሮ ለመውጣት በድግግሞሽ ኬኒያ ፓሊስ ሳጥን ይደረሱ የነበሩት ንግድ ባንኮች በመጨረሻም 79ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። ከቀኝ አረጋሽ ይዛ ገብታ የሰጠቻትን ኳስ መሳይ አጠገቧ ለነበረችው ሰናይት ቦጋለ ስትሰጣት አማካዩዋ በፍጥነት ነፃ ቦታ ለተገኘችው ሴናፍ አቀብላት አጥቂዋ በመድረኩ ስድስተኛ ግቧን አስቆጥራ ቡድኗን መሪ አድርጋለች።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ ሌላ ያለቀለትን አጋጣሚ አግኝታ መጠቀም ሳትችል ቀርታ በመጨረሻም ጨዋታው 1ለ0 ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣርያ ወድድር አሸናፊ በመሆኑ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ምስራቅ አፍሪካን ይወክላል።