ዋልያዎቹ ነገ በአዲስ አበባ የልምምድ ጨዋታ ሊያደርጉ ነው

ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎቹ ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኙት ዋልያዎቹ የልምምድ ጨዋታ ሊያደርጉ ነው።


በቀጣይ ሳምንት ከታንዛንያ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስቴድየም ከኢትዮጵያ መድን ጋር ተመሳሳይ የልምምድ ጨዋታውን ያከናወነው ቡድኑ በነገው ዕለት ከቀትር በኋላ በአበበ ቢቂላ ስቴድየም የሱዳን አቻውን ለመግጠም ቀጠሮ ተይዞለታል።

ከኒጀር እና አንጎላ ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ በአዲስ አበባ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ የሚገኘው የሱዳን ብሄራዊ ቡድን ባለፈው ግንቦት ወር በሳውዲ ዓረብያ ከኢትዮጵያ ተጋጣሚ ታንዛንያ ጋር ሁለት የአቋም መለክያ ጨዋታዎች ማከናወኑ ይታወቃል። በክዌሲ አፕያ የሚሰለጥነው ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ማውሪታንያ እና ደቡብ ሱዳንን በተከታታይ ማሸነፉም ይታወሳል።


በነገው ዕለት ለተመልካች ዝግ ሆኖ ሁለተኛ የልምምድ ጨዋታውን ለማድረግ በዝግጅት ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድናችን የመጀመርያ ጨዋታውን ከታንዛንያ ጋር ነሐሴ 29 ቀን፤ ሁለተኛ ጨዋታውን ደግሞ ጳጉሜ 4 ቀን ከኮንጎ ዲ.ሪ ጋር ዳሬ ሰላም ብሔራዊ ስታዲየም የሚያደርጉ ይሆናል።