ስሑል ሽረ ካሜሩናዊ ግብ ጠባቂ ለማስፈርም ተስማማ

የቀድሞ የአሻንቲ ኮቶኮ ግብ ጠባቂ የስሑል ሽረ አስራ አምስተኛ ፈራሚ ለመሆን ከስምምነት ደርሷል።


ከሳምንታት በፊት አላዛር አድማሱ፣ ጃፋር ሙደሲር እና ጥዑመልሳን ኃይለሚካኤል ያስፈረሙት ስሑል ሽረዎች አሁን ደግሞ ካሜሩናዊው ግብ ጠባቂ ሞይስ ፖዋቲ በማስፈረም በዝውውሩ በንቃት መሳተፋቸውን ቀጥለዋል። በሀገሩ ክለብ ዩኒየን ዱዋላ የእግር ኳስ ሂወቱ የጀመረው ይህ የሀያ ስምንት ዓመት ግብ ጠባቂ ከዚ ቀደም በዩናይትድ ስቴስት ሁለተኛ የሊግ እርከን በሚሳተፈው ኮሎራዶ ስፕሪንግስ ስዊችባክስ የሁለት ዓመት ቆይታ የነበረው ሲሆን ከዛ ቀጥሎ ለካሜሩኑ ክለብ ፎርቱና ደ ምፎው ከተጫወተ በኋላ በ2022 የጋናው አሻንቲ ኮቶኮ ተቀላቅሎ ላለፉት ዓመታት በኩማሲው ክለብ ቆይታ አድርጓል። አሁን ደግሞ ከጋናው ክለብ ጋር ያለውን ውል መጠናቀቁን ተከትሎ የህክምና ምርመራውን አገባዶ ስሑል ሽረን ለመቀላቀል ተስማምቷል።


ከክለቡ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ላለፉት ሳምንታት በሽረ እንዳስላሰ ከተማ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ የቆየው ክለቡ ከቀናት በፊት ወደ መቐለ ከተማ በማቅናት በከተማው ዝግጅቱን ማከናወኑን ቀጥሏል።