ስኬታማው አሰልጣኝ ከዛሬው ድል በኋላ ምን አሉ ?

👉 “ተጫዋቾቼ ላደረጉት ተጋድሎ አመሰግናለሁ”

👉 “ሀያ አምስት ዋንጫዎች በሀገሬ አሳክቻለሁ የዛሬው ዋንጫ ደግሞ ለኔ ልዩ ነው”

👉 “እንደኔ ብዙ ተቸግሮ የሴቶች እግር ኳስ ነገ ጥሩ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብሎ ለለፋ ሰው እንዲህ አይነት ድል ማግኘት እንደ ትንሳኤ ነው”

በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ቡድኑን ለካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ያሳለፈ የመጀመርያው አሰልጣኝ በመሆን ደማቅ ታሪክ የፃፈው እና ዛሬ በእግር ኳስ ሕይወቱ ሃያ አምስተኛ ዋንጫውን ያነሳው አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ከታሪካዊው ድል በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያው ቶማስ ቦጋለ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

ስለ ዛሬው ድል

ዛሬ ከሌላው ጊዜ በተለየ ነቃ ብለን የተጫወትንበት እና እጅግ ደስ የሚል ነው። ተጫዋቾቼ ላደረጉት ተጋድሎ አመሰግናለሁ። የተነገራቸውን ነገር በመስማት ነቅተው ታሪክ መስራት እንዳለባቸው አምነው ነው የገቡት። ሌላው የአራት ዓመት ቁጭቴ ነው ሦስት ዓመት ያለቀስኩበት ነገር ነው። ከዚህ በፊት በብዙ ነገር ተበድለናል፤ በዳኛ ጫና እና ሌላም እንግልት ነበር። ዘንድሮ ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተጋፍጦ ውድድሩን በሀገራችን እንዲካሄድ ማድረጉ በድጋሚ ማመስገን እፈልጋለሁ። የዛሬው የሻምፕዮንነት ድል በሕይወቴ ካገኘኋቸው ልዩ ድሎች አንዱ ነው። ዛሬ ደግሞ ቀኑ ሃያ ሦስት ነው ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ የልቦናየን አሳክቶልኛል። ሃያ አምስት ዋንጫዎች በሀገሬ አሳክቻለሁ የዛሬው ዋንጫ ደግሞ ለኔ ልዩ ነው።

በግሌ ለአፍሪካ መድረክ ሳልፍ ለሁለተኛ ጊዜዬ ነው፤ ከአስራ ሁለት ዓመት በፊትም በተመሳሳይ ሀገሬን አገልግዬ አሳልፍያለሁ። አሁን ደግሞ በክለብ ደረጃ ማሳካቴ በጣም ደስ ብሎኛል።


ስለ የእግር ኳስ ሕይወት ስኬቱ

እግዚአብሔር ይመስገን ሁሉም ነገር አሳክቻለሁ ብዬ አስባለሁ። በሕይወቴ ማሳካት የምፈልገው ይሄ ነበር። እንደኔ ብዙ ተቸግሮ የሴቶች እግር ኳስ ነገ ጥሩ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብሎ ለለፋ ሰው እንዲህ አይነት ድል ማግኘት እንደ ትንሣኤ ነው። እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን የምመኘውን ነገር አሳክቻለሁ።