አርባምንጭ ከተማ ሁለት የውጪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማማ

ዳግም ወደ ሊጉ ያደገው አርባምንጭ ከተማ ናይጄሪያዊ እና ዩጋንዳዊ ተጫዋቾች ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ተስማምቷል።

በአሠልጣኝ በረከት ደሙ እየተመራ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ያረጋገጠው የከፍተኛ ሊጉ ሻምፒዮን አርባምንጭ ከተማ የአሠልጣኙን ውል ካራዘመ በኋላ የነባር ተጫዋቾችን ውል በማደስ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ እየቀላቀለ ይገኛል። በክለቡ መቀመጫ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኘው ቡድኑ ሁለት የውጪ ሀገር ተጫዋቾችን ለማስፈረም መስማማቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው የመጀመሪያው ተጫዋች ቻርለስ ሪባኑ ነው። ናይጄሪያዊው የአማካይ መስመር ተጫዋች ከአራት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያን እግርኳስ ከተዋወቀ በኋላ በሀምበርቾ፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ እና አዳማ ከተማ ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን አሁን አዞዎቹን በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅሏል።

ሁለተኛው ተጫዋች ዩጋንዳዊው ብሪያን አሄብዋ ነው። በሀገሩ ክለቦች ምባራራ ሲቲ እና ኬሲሲኤ ያሳለፈው የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ከሳምንታት በፊት ክለቡ ኪታራ ከመቻል ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ሲያከናውን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረ ሲሆን አሁን በቋሚነት ለኢትዮጵያ ክለብ ለመጫወት አዲስ አበባ ገብቷል።