ለሚዲያ ዝግ የነበረው ጨዋታ በዋልያዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታቸው ይረዳቸው ዘንድ ከሱዳን አቻቸው ጋር የልምምድ ጨዋታ ያደረጉት ዋልያዎቹ ድል ቀንቷቸዋል።

በቀጣይ ሳምንት ወደ ዳሬ ሰላም አቅንቶ ከታንዛኒያ እና ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ላለበት ጨዋታ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለሚዲያ ዝግ የሆነ ሠላሳ፣ ሠላሳ ደቂቃ የወሰደ የልምምድ ጨዋታ አድርጓል።

በመጀመርያው አጋማሽ ግብ ጠባቂ – ሰዒድ ሀብታሙ ተከላካይ – ብርሃኑ በቀለ፣ ያሬድ ባየህ፣ ፈቱዲን ጀማል፣ ያሬድ ካሳዬ አማካይ -ጋቶች ፓኖም፣ አብነት ደምሴ፣ ወገኔ ገዛኸኝ አጥቂ – ከነዓን ማርክነህ፣ ምንይሉ ወንድሙ፣ ቸርነት ጉግሳ ሆነው በገቡበት ስብስብ ውስጥ በጨዋታው 20 ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ በቢኒያም ዐይተን እንዲቀየር ሆኗል። በአጋማሹም ውጤት ቸርነት ጉግሳ እና ቢንያም ዐይተን ባስቆጠሯቸው ጎሎች ኢትዮጵያ 2-0 እየመራች ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ቢንያም ዐይተንን ብቻ አስቀርተው በግብ ጠባቂነት ፍሬው ጌታሁን ተከላካይ – ረመዳን የሱፍ፣ ፍሬዘር ካሳ፣ ሚሊዮን ሰለሞን፣ ሱሌይማን ሀሚድ አማካይ – በረከት ወልዴ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ቢንያም በላይ አጥቂ – አዲስ ግደይ፣ ቢኒያም ፍቅሬ እና ቢኒያም ዐይተንን ተጠቅመዋል። በጨዋታው መጠናቀቂያም ቢኒያም ዐይተንን በአብዱልከሪም ወርቁ ቀይረው አስገብተዋል። በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጎል ሳይቆጠር ወጥተዋል። ለሁለት ተከፍሎ በተካሄደው ጨዋታ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱን ተከላካይ አማኑኤል ተርፉን የዋልያዎቹ አለቃ ሳይጠቀሙት ቀርተዋል።

በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ የልምምድ ጨዋታ አድርጎ 4-0 ማሸነፉ ሲታወስ ቡድኑ በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ የነበረውን የዝግጅት ጊዜ በማጠናቀቅ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ማረፊያውን በጁፒተር ሆቴል በማድረግ በቀሩት ቀናት ሲዘጋጅ ቆይቶ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ሰኞ አልያም ማክሰኞ ወደ ዳሬ ሰላም የሚያቀና ይሆናል።