አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ መግለጫ ሰጥተዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊታችን ረቡዕ ከታንዛኒያ እና ቀጣይ ሰኞ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ለሚያከናውናቸው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች ያደረገውን ዝግጅት አስመልከቶ ዋና አሰልጣኙ ገብረመድኅን ኃይሌ መግለጫ ሰጥተዋል

በፌደሬሽኑ ጽ/ቤት የተሰጠው መግለጫ ላይ አሰልጣኙ ዝግጅታቸውን በተመለከተ ተከታዩን ሀሳብ በመስጠት ነበር የጀመሩት ፤

“ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅት ጀምረን 13 ቀናትን አስቆጥረናል። ወደኋላ ላይ አዲስ ግደይ ሲጨመር 29ኛ ተጫዋች ይሆናል። ከተጠሩት መካከል አንዳንዶቹ ከሀገር ውጪ ስለነበሩ እና እዚህ ከነበሩትም እንደነ ከነዓን ያሉ ለሙከራ የሄዱ ስለነበሩ ዝግጅት ስንጀምር 21 ተጫዋቾች ነበሩ ፤ አሁን 25 ናቸው ሁለቱን በመቀነስ 23ቱን ይዘን እንሄዳለን። አቤል ያለው እና አቡበከር ናስር በሕመም ምክንያት መጫወት እንደማይችሉ ነግረውናል። መስፍንም ጥቂት ቀናትን ከሠራ በኋላ እሱም በሕመም ምክንያት ከቡድኑ ተለይቷል። ተመስገን ብርሃኑ ለሙከራ ወደ ግብጽ ሄዷል። ፕሮፌሽናል ሆነው እንዲጫወቱ የምንፈልገው ስለሆነ የሙከራ ዕድል ሲያገኙ ፍቃድ ሰጥተናቸው ሄደዋል። ብዙ ተጫዋቾች ፕሮፌሽናል ተጫዋች ሲሆኑ ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ እና ብዙ ለውጥ ማምጣት ስለሚችሉ የእነሱ ብቻ ሳይሆን እዚህ ላሉትም ልምድ ያካፍላሉ ብለን እናስባለን። እንደ አጋጣሚ ብዙ ተጫዋቾች የሉንም። ጥሩ ደረጃ ይደርሳል ብለን የጠበቅነው አቡበከር ናስርም እስካሁን በተለያዩ ምክንያቶች ቡድኑን አልተቀላቀለም አቤልም በስተመጨረሻ ታሟል። ሌሎቹ ሚሳካላቸው ከሆነ ሙከራ እያደረጉ ስለሆነ እናበረታታለን። ሰኞ ጠዋት ነው የምንጓዘው። ዝግጅቱን ስንጀምር ወቅቱ አስቸጋሪ ስለነበር ትንሽ አስቸግሮናል። አስቸጋሪ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የ”ኦፍ ሲዝን” ወቅት መሆኑ ነው። ቲሞች ወደ ዝግጅት የሚገቡበት እና አንዳንዶቹ ጭራሽ ያልጀመሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከሚገባው በላይ የአካል ብቃት የሠሩ ይኖራሉ እና በጣም የተለያየ ደረጃ ላይ የደረሱ ተጫዋቾችን ይዘን ነው የጀመርነው። እኔ ከመጣሁ ጀምሮ እስከዛሬ ከውድድር ነበር የምወስዳቸው እና ጥሩ ነበር። አሁን ግን በጣም መጥፎ ጊዜ ላይ ስለሆነ ተጫዋቾቹን ቴስት ማድረግ ነበረብን ፤ ቴስት ስናደርግ ብዙዎቹ የአካል ብቃታቸው ወርዶ ነው ያገኘነው እነሱን ማሠራት ነበረብን የሠሩትን ደግሞ ባላንስ ማድረግ ነበረብን። ይሄም የቡድን ሥራ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን እንዳንሠራ አድርጎናል። በ12 እና 13 ቀናት የአካል ብቃትም የቲም ወርክም ለመሥራት ሞክረናል። ሦስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርገናል ፤ የውጪ ጨዋታ ለማግኘት በተለይም በአቶ ኢሳይያስ ጂራ አማካኝነት ጥረት ተደርጓል። ግን ብዙዎቹ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ስላሏቸው እና እየተንጠባጠቡ ስለሚገቡባቸው አስቸግሮናል። መጨረሻ ላይ የተገኘው የሱዳን ቡድን ነበር ፤ እነሱ ጋርም ሙሉ ስብስብ ስላልነበር አንዴ እሺ ሲሉ ፥ አንዴ ደቂቃው ይቀነስልን ሲሉ የነበር ቢሆንም ሁለት ሠላሳ ደቂቃዎችን የመጫወት ዕድል አግኝተናል። ከድሬዳዋ እና ከመድን ጋርም ጨዋታዎችን አድርገናል። ከየጨዋታው ብዙ ትምህርት እያገኘን ተጫዋቾችም እየተዋሃዱ ነው። ለምሳሌ ትናንት ያየሁት አንድ ልንከተለው የሚገባ አጨዋወት ተከትለው በዛ መንገድ መጫወት መቻላቸው ራሱ አንድ ዕድገት ነው ብዬ ነው የማስበው። ምንም እንኳ ሁለት 30 ደቂቃ ቢሆንም ቡድናችን ላይ ምንም ሙከራ አልተደረገም ፤ ይሄ ለየት ያደረገዋል። ሁለተኛ የነጠቅናቸው ኳሶችን ቶሎ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በማድረስ ረገድ የተሻለ ነበር አሁንም መሻሻል ያለበት ነገር ቢኖርም ፤ አጨራረስ ላይ አሁንም ችግሮች አሉ እሱም ይሻሻላል ብለን እናስባለን። “ሀይ ፕሬስ” በመጫወት ግን ጥሩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ከዛ ጎን ለጎን እንደየ ተጋጣሚያችን የሚሆን የምንጫወትበት ስታይል ይዘን መሄድ አለብን ስለዚህ እሱን ለማስረዳት ጥረት አድርገናል። ነገ አንድ ልምምድ እንሠራለን ፤ ከነገ ወዲያ ልምምድ ሳንሠራ ነው ወደ ስፍራው የምናቀናው እዛው ነው ምንሠራው።”


ዋና አሰልጣኙ ይህንን ሀሳቡ ከሰጡ በኋላ በስፍራው ከተገኙ ጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

አቡበከር ናስር ቡድኑን ያልተቀላቀለው በጉዳት ወይስ በሌላ ምክንያት…?

“ይሄ የጉዳት ጉዳይ ለማጣራት ጥረት አድርጉ የሚል ነው። አቤል ለፌዴሬሽኑ ማስረጃ ልኳል ፤ የታከመበትን እና ጉዳቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ እነሱም ለእኔ ልከውልኛል ፤ ሌላ ርቀት መሄድ አስፈላጊ ስላልነበር ማለት ነው። የአቡበከርም ዘግይቶ ነው የመጣው መጀመሪያ እሺ ብሎ ክለቡ ፈቅዶለት እንደነበር ነው ከፌዴሬሽኑ የደረሰኝ። ከዛ በኋላ ግን በመጨረሻ ሰዓት ነው ጉዳት እንደነበረበት እና መምጣት እንደማይችል በቮይስ የላከላቸው። በጥልቀት ገብተን ለማጣራት ያደረግነው ጥረት የለም። ለወደፊቱ ግን መጣራት ያለበት ነገር ይኖራል በትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለው ወደፊት ከታወቀ እና ሌላ ነገር ከሆነ ምናልባትም ለተጫዋቹም ለሌላውም ጥሩ የሚሆን አይመስለኝም። እንደማስበው ግን ጉዳት እንዳለው ነው የተረዳሁት።”

ስለ ቴክኒክ ስታፉ…?

“ብዙ ጊዜ የሚነሳ ጥያቄ ነው። ቲሙ እንደ ቲም አስቸጋሪ ሁኔታ እስካልገጠመው ድረስ በዚህ ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል። አስፈላጊ ነው ብሎ ባመነበት ደግሞ መሟላት ያለበት ነገር እንዲሟላ ይጠይቃል። አንዳንድ ሁኔታዎችን ለማጣራት ብዙ ጥረት እየተደረገ ነው። ቪዲዮ አናሊስት አለ ፣ የአካል ብቃት አሰልጣኝ አለ። ግዴታ አይደለም ፤ ይሄ እንደመስፈርት ሊያዝም አይገባም። አስፈላጊ ሆኖ ስናገኘው እናሟላለን። ብዙ ጥረቶች እያደረግን ነው ለዛ ግን ብቁ የሆነ ሰው ያስፈልጋል። ዝም ብለን ከዚህ ቀደም እዚህ ስለነበሩ በሚለው አይደለም የምናመጣው። እዚህ የነበሩት በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እናውቃለን አንዳንዶቹ እዚህ ይሠሩ የነበሩ ክለብ ውስጥ እየሠሩ ነው። ስለዚህ ከተለያየ አንግል ነው የምናየው ባሕሪ አለ ፣ ብዙ ነገሮችም አሉ። ጥሩ የሆነ ብቃት ያለው ሲገኝ ይመጣል። ቲሙ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳሉበት ይታወቃል ግን ያን ያህል ችግር የፈጠረበት ነገር ስለሌለ ቀጥለናል። ወደፊት ይሟላል አሁንም ልናሟላ እንችላለን ብዬ ነው የማስበው ፤ እንደ ዋና ነገር ግን አይታይም።

ባደረግካቸው አራት ጨዋታዎች ቡድንህ አንድ ጎል ብቻ ነው ያስቆጠረ ይሄ በምን ይቀረፋል…?

“አራቱንም ጨዋታ ከሜዳ ውጪ ተጫውተህ ጎል ለምን አላገባህም የሚባል ነገር ምናልባት ካለን ተጨባጭ ሁኔታ ካለመረዳትም ይሆናል። አንደኛ አጠቃላይ ሀገሪቱ ላይ ያለው የአጥቂ ችግር ነው። እንደ ቲም ተንቀሳቅሰህ ማግባት ካልቻልክ ዘጠኝ ቁጥር አጥቂ የማግኘት ዕድላችን በጣም ጠብቧል። ለብዙ ዓመታት ብታዩ የውጪ ሀገር ተጫዋቾች ናቸው ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆነው የሚጨርሱት። ይህ ሌላ ምክንያት የለውም የአጥቂ ደረጃ ብቃታችን ነው። ዘጠኝ ቁጥር አጥቂ በዓለም ደረጃ እየጠፋ ነው። ወደ እኛ ሀገር ሲመጣ ደግሞ በጣም በጣም የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰናል። ስለዚህ እነዚህን አጥቂዎች ለመፍጠር በአንድ ጀምበር የሚሆን ሳይሆን ለዓመታት በጣም ብዙ ሥራዎችን ይፈልጋል። ከፕሮጀክት ጀምሮ መሠራት ያለበት እንጂ በአንድ የተወሰነ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ ይመጣል ማለት አይቻልም። ነገር ግን ባለህ ስለምትወዳደር ሲስተምህ እንዲያጠቃ ማድረግ አንዱ አማራጭ ነው። በጋራ ማጥቃት እንዲቻል ኦፌንሲቭ የሆነ አጨዋወት መጫወት ያስፈልጋል። ከኋላ የሚነሱ ሰዎችን ማድረግ ያስፈልጋል። ሲስተምህ እዛ ላይ እንዲችል ማድረግ ነው እንደ ቲም መንቀሳቀስ እና ማጥቃት ማለት ነው። ያንን መፍጠር ካልተቻለ…ፕሮሰሱ አለ ይደርሳሉ ግን እንደ ጅቡቲ ካሉት ጋር ስንገናኝ እንኳ በጣም ብዙ ኳስ ነው ያመከነው ትናንትም ያለቀላቸውን ሦስት ንጹህ ጎል ነው የተሳተው። ይሄ አሁን በአጭር ጊዜ የሚቀረፍ አይደለም። ከአመጋገብ ጀምሮ ወደኋላ ተመልሰን ብዙ የምንሠራቸው ነገሮች አሉ። በአጭር ጊዜ የአጥቂ ችግራችንን ለመቅረፍ እንችላለን ብዬ ለመናገር ይከብደኛል።


በሜዳቸው መጫወት አለመቻላቸው ስላለው ተጽዕኖ?

“በሜዳ አለመጫወታችን ማንም እንደሚረዳው ጉዳት አለው። ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለቱን በሜዳችን ብናደርግ ኖሮ ቢያንስ አራት ነጥብ እናገኝ ነበር ፤ ምንም ጥርጥር የለውም። የአየር ሁኔታ ፣ ደጋፊያችን ፣ ከተጽዕኖ ውጪ የሆነ ጨዋታ መጫወት ፤ በየሜዳው የሚያጋጥሙ ተጽዕኖዎች አሉ የዳኛ ምናምን እነዚህ ሁሉ ጥቅማቸው ብዙ ነው በሜዳችን ሲሆን። ስለዚህ ለማሸነፍ ቅርብ ነው የምንሆነው። አውሮፓዎች ሆም ኤንድ አዌይ ወደ ማስቀረት ደርሰዋል ለእንደ እኛ ዓይነት ሀገር ግን የአየር ሁኔታ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። በሜዳችን ባለመጫወታችን የምናጣው ነገር በጣም ብዙ ነው።