ዐፄዎቹ ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ፋሲል ከነማዎች አንድ የውጪ ዜጋን ጨምሮ አምስት ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ መሪነት በአዳማ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየከወኑ የሚገኙት ዐፄዎቹ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ራሳቸውን ለማጠናከር ይረዳቸው ዘንድ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረማቸውን ቀጥለው አሁን ላይ ደግሞ ተጨማሪ አምስት ተጫዋቾችን ማስፈረማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ቡድኑን የተቀላቀለው ቀዳሚው ተጫዋች የ26 ዓመቱ ዩጋንዳዊ አጥቂ ማርቲን ኩዛ ነው ፤ በሀገሩ ለሚገኙት ኬ ሲ ሲ ኤ ፣ ኤ ኤስ ቪላ ፣ ኤክስፕረስ እና ቫይፐርስ የተጫወተው አጥቂው ከሀገር ወጥቶም ለደቡብ አፍሪካዎቹ ስታርስ እና ሮያል ኤግልስም እንዲሁ ስለመጫወቱ የግል ማህደሩ ያሳያል።

ቡድኑ ከዩጋንዳዊው አጥቂ በተጨማሪ የሙከራ ዕድል ሰጥቷቸው ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል ጥሩ ብቃትን አሳይተው አሰልጣኙን ማሳመን የቻሉ አራት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

በሻሸመኔ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና መጫወት የቻለው ተከላካዩ ተመስገን ካስትሮ ባለፉት ዓመታት ከሜዳ ካራቀው የጉልበት ጉዳት መልስ ዳግም ወደ ሊጉ የሚመልሰውን ዝውውር ሲፈፅም በቡራዩ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተጫወተው አጥቂው አንዋር ሙራድ ፣ በአውስኮድ እና ባለፈው የውድድር ዘመን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቆይታ የነበረው አማካዩ ኤፍሬም ሐይሉ እና በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ፣ ቦሌ እና ዳንግላ እንዲሁም በጉለሌ ክፍለ ከተማ አጥቂ በመሆን ያገለገለው አትርሳው ተዘራ የፋሲል ከነማ ሌሎቹ አዳዲስ ፈራሚዎች ናቸው።