ከዋልያዎቹ ጋር አብሮ ወደ ታንዛኒያ ያልተጓዘው ፍሬዘር ካሳ ወደ ስፍራው ይሄዳል ወይስ?
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነሐሴ 29 ቀን ከታንዛኒያ ጳጉሜ 4 ቀን ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር በታዛኒያ በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ጨዋታውን እንደሚያደርግ ይታወቃል።
ለአስራ አምስት ቀናት ያህል ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየው ቡድኑ አማኑኤል ተርፉ እና አብዱልከሪም ወርቁን በመቀነስ ዛሬ ረፋድ ላይ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ዳሬ ሰላም ያቀናል ተብሎ ሲጠበቅ ፍሬዘር ካሳ ከፓስፖርት ጋር በተያያዘ ሳይጓዝ መቅረቱን አስቀድመን መረጃውን ማድረሳችን ይታወቃል። ታዲያ ፍሬዘር ወደ ዳሬ ሰላም ያቀናል ወይስ ቡድኑ በ22 ተጫዋቾች ሁለቱን ጨዋታ ይከውናል የሚለውን ሶከር ኢትዮጵያ ተከታዮን መረጃ አጠናክራለች።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚመለከታቸው አካላት ተጫዋች ፍሬዘር ካሳ ወደ ታንዛኒያ በሚያቀናበት ሁኔታ ዙርያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያደረጉት ንግግር ተሳክቶ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታዎች በማጠናቀቅ ዛሬ ማምሻውን እንደሚሄድ ታውቋል።