ትውልደ ኢትዮጵያዊው ወደ ጣልያን አምርቷል

ጄኖዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊውን አማካይ የመግዛት አማራጭን ባካተተ የውሰት ውል አስፈርሟል።

ባለፈው የውድድር ዓመት ከእስራኤሉ ታላቅ ክለብ ማካቢ ሀይፋ ጋር ቆይታ የነበረው ቤተ እስራኤላዊው የአስራ ስምንት ዓመት አማካይ ሊዮር ካሳ በአንድ ዓመት የውሰት ውል የጣልያኑን ክለብ ጄኖዋን ተቀላቀለ።


ከቀናት በፊት የህክምና ምርመራውን በተሳካ ሁኔታ ካጠናቀቀ በኋላ 300,000 ዩሮ የውሰት ክፍያ እና 2.5 ሚልዮን ዩሮ የመግዛት አማራጭ ባካተተው ስምምነት ወደ ጣልያኑ ክለብ ያመራው ይህ ተስፈኛ ተጫዋች በታዳጊ ቡድን ደረጃ በሃፖል ካታሞን እና ሃፖል ጄሩሳሌም ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ በዋናው ቡድን ደረጃ በአሳዳጊ ክለቡ ሃፖል ጄሩሳሌም እና በታላቁ ክለብ ማካቢ ሃይፋ ቆይቷ አድርጓል።

በእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘንድ ትልቅ ተስፋ እንዳለው የሚነገርለት ይህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ 185 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ቁመቱ፣ በሁለቱም እግሮች መጫወት መቻሉ እና አካላዊ ጥንካሬው ዋነኛ መገለጫዎቹ እንደሆኑ ይነገርለታል።

አማካዩ ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ እየሰራ ከሀያ ዓመት በታች ተጫዋቾች በሚሳተፉበት Primavera 1 ሊግ ይሳተፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በውድድሩም በኮሞ ከሚገኘው የአስራ ሰባት ዓመቱ አማካይ ገላና አፍሮንቲ፤ በቅርቡ ወደ ሞንዛ ካቀናው ተከላካዩ እንድሪስ ስካራሜሊ እና በሄላስ ቬሮና የሚገኘው አጥቂው ዮናስ ዛምብያሲ ቀጥሎ በወጣቶቹ ሊግ የሚሳተፍ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ይሆናል።

በጣልያን የታችኛው የሊግ እርከን በርከት ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በሴሪ ‘D’ በሚሳተፉ ክለቦች ውስጥ የሚገኙት ዳዊት ፎሲ፣ ናትናኤል ኮስታንቲኒ፣ ወንድማገኝ ቴረቪሳን፣ መታሽ ጋፉሪ እና ሀብታሙ ጋስቲ በቀጣይ ሳምንት ለሚጀምረው አዲሱ የውድድር ዘመን በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።