በዝውውር መስኮቱ ከዚህ ቀደም ሁለት ግብ ጠባቂዎችን ያስፈረሙት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ ሦስተኛ ግብ ጠባቂያቸውን የግላቸው አድርገዋል።
ቀደም ብለው በከፍተኛ ሊጉ ንብ ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፈው የቀድሞ ግብ ጠባቅያቸው ሶፎንያስ ሰይፈ እና ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት ከላይቤርያው ክለብ ሔቨን ኢለቨን ያሳለፈው እና በቅርቡ በሶሻል ሳይንስ የመጀመርያ ዲግሪው ያገኘው ሴራልዮናዊው ግብ ጠባቂ አልፋ ኖህ ሴሳይ ለማስፈረም የተስማሙት መቐለ 70 እንደርታዎች አሁን ደግሞ ምሕረትአብ ገብረህይወትን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።
በ2009 ዓ.ም ደደቢትን ለቆ መቐለ 70 እንደርታ ከተቀላቀለ በኋላ በክለቡ የአራት ዓመታት ቆይታን አድርጎ በ2013 ከቡድኑ ጋር ተለያይቶ በመቻል፣ በከፍተኛ ሊጉ ስልጤ ወራቤ እና ሀድያ ሆሳዕና ቆይታ የነበረው ይህ ግብ ጠባቂ ከነብሮቹ ጋር በስምምነት ተለያይቶ ከዓመታት በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሶ ለመጫወት ከስምምነት ደርሷል።
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ዜና ሐምሌ 30 በመቐለ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረው ቡድኑ በነገው ዕለት ለተጨማሪ ዝግጅት እንዲሁም የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ለማድረግ ወደ አዳማ ከተማ እንደምያቀና ለማወቅ ተችሏል።