የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መቻል የአሰልጣኝ ሽግሽግ ሲያደርግ 11 ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚሳተፈው መቻል አሰልጣኝ መቶ አለቃ ስለሺ ገመቹን ዋና አሰልጣኝ ሲያደርግ አስራ አንድ አዳዲስ እና ስምንት ነባሮችን ደግሞ አስፈርሟል።

የ2016 የውድድር ዘመንን በ53 ነጥቦች 4ኛ ላይ ተቀምጦ የቋጨው መቻል ለቀጣዩ ዓመት ቡድኑን ለማጠናከር በማሰብ ረዳት የነበረውን አሰልጣኝ መቶ አለቃ ስለሺ ገመቹን በድጋሚ ወደ ቀደመ ዋና አሰልጣኝነቱ የሾመው ሲሆን ቡድኑ አስራ አንድ አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም ስምንት ነባሮች ደግሞ ውላቸው ታድሷል።

አዳዲስ ፈራሚዎችን ስንመለከት የቀድሞዋ የንግድ ባንክ ፣ ድሬዳዋ እና አርባምንጭ አጥቂ ፎዚያ መሐመድ ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማዋ አማካይ ብዙዓየሁ ጸጋዬ ፣ በሲዳማ ቡና በቀኝ ተከላካይነት የተጫወተችው ሕይወት ዳንኤል ፤ በአዲስ አበባ ድሬዳዋ እና ኤሌክትሪክ የምናውቃት የመሐል ተከላካይ አብነት ለገሠ ፤ በደደቢት ፣ ንግድ ባንክ እና ዓምና በኤሌክትሪክ ቆይታ የነበራት አማካይ ትዕግስት ያደታ ፤ በአቃቂ ፣ ሀዋሳ ፣ ድሬዳዋ እና ንግድ ባንክ የመሐል ተከላካይ የነበረችው ብርቄ አማረ ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማዋ አጥቂ ትዕግሥት ወርቄ ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ አጥቂ ሆና ያገለገለችው ቤቴልሔም መንተሎ ፣ የሀዋሳ እና አርባምንጭ አማካይ በአርባምንጭ ሀዋሳ አማካይ የነበረችው ትውፊት ካዲዮ  ፣ አማካይዋ መሠረት ማሞ ከአዲስ አበባ እና ተከላካይዋ ሰናይት ሸጎዬ ከአዳማ ክለቡን መቀላቀል የቻሉ አዳዲሶቹ ተጫዋቾች ሆነዋል።

ክለቡ የስምንት ነባሮችን ውል ሲያራዝም ታደለች አብርሃም ፣ ትርሲት ወንድወሰን ፣ ስርጉት ተስፋዬ ፣ አበባየሁ ጣሰው ፣ ባንቺየሁ ደመላሽ ፣ ፌቨን ተሾመ ፣ ጽዮን ፈየራ እና ስንታየው ሂርኮ ለተጨማሪ ዓመት በቡድኑ ይቆያሉ።