የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ ከተማ ወደ ዝውውር ገብቷል

በአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረ የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ የአራት ነባሮችን ውልም አድሰዋል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ ሀዋሳ ከተማ ነው። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በ57 ነጥቦች ከሻምፒዮኑ ንግድ ባንክ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ የቻለው የአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረው ክለብ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ተጠናክሮ ለመቅረብ ይረዳው ዘንድ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአራቱን ነባሮች ውልም አራዝሟል።

ቡድኑን የተቀላቀለችው የመጀመሪያ ፈራሚ የግራ መስመር አጥቂዋ የምስራች ላቀው ናት። መቻል ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ አዳማ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫውታ ያሳለፈችባቸው ክለቦች ናቸው። ሌሎቹ ፈራሚዎች በአርባምንጭ ከተማ ላለፉት ስድስት ዓመታት በግራ መስመር ተከላካይነት እና በአምበልነትም ጭምር ቡድኑን የመራችው ለምለም አስታጥቄ ፣ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከተገኘች በኋላ በአርባምንጭ ፣ ባህር ዳር እና የተጠናቀቀውን ዓመት በመቻል ጥሩ የውድድር ዘመን በማሳለፏ የዓመቱ ምርጥ 11 ተጫዋቾች ውስጥ ተካትታ የነበረችው አማካይዋ ቤቴልሔም ግዛቸው እና በቦሌ ክፍለ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ በተከላካይነት ያገለገለችው ከአምላክነሽ ሀንቆም ሌላኛው የቡድኑ አዲሷ ተጫዋች ሆናለች።

ቡድኑ ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ በቡድኑ ውስጥ የነበሩትን የቀኝ መስመር ተከላካዩዋ ፀሐይነሽ ጁላ ፤ የአጥቂዎቹን ረድዔት አስረሳኸኝ እና ታሪኳ ጴጥሮስ እንዲሁም የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነችውን በረከት ጴጥሮስን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሟል።