የዋልያዎቹ እና የታይፋ ኮከቦቹ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

ምሮኮ በ2025 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ 8 ተደልድለው የሚገኙትን ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያን ያገናኘው መርሐግብር 0ለ0 ተቋጭቷል።

የካፍ ዝቅተኛ መስፈርትን ባሟላው ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ምሽቱን የተደረገውን ጨዋታ የ40 ዓመቱ ሴናጋላዊ የመሐል ዳኛ ኢሳ ሳይ መርተውታል። ከዕለቱ ዳኛ ፊሽካ መነፋት አንስቶ ከራስ ሜዳ በሚደረጉ ቅብብሎች ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል በመድረሱ የተዋጣላቸው ዋልያዎቹ በአግባቡ ጨዋታውን በመቆጣጠር ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በወጥነት ቢደርሱም የጠሩ አጋጣሚዎችን ፈጥረው ግን ለመመልከት አልታደልንም።

የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደባቸው እና ፈጠን ባሉ ሽግግሮች የሚነጥቋቸውን ኳሶች ወደ መስመር አጋድለው በረጅሙ በመጣል ማጥቃትን መርጠው የተጫወቱት የታይፋ ኮከቦቹ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የግብ ዕድሎችን ከማግኘት አንፃር በተመሳሳይ ዐይናፋሮች ነበሩ። የጨዋታው ግለት ሜዳ ላይ ከፍ ያለ መልክ እንደነበረው መመልከት የቻልን ቢሆንም ከግብ መረብ ጋር ኳስን ከማዋሀድ አኳያ ሁለቱም ቡድኖች እጅጉን ደካሞች ነበሩ።

23ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ ያሬድ ካሳዬ ከርቀት ሞክሮ ዒላማዋን ሳትጠብቅ ኳሷ የወጣችበት አጋጣሚ ወደ ግብ የተመታች ነገር ግን ዒላማዋን ያልጠበቀች ዕድል ሆና አጋማሹም ያለ ጎል ተጋምሷል።

 

ከዕረፍት መልስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቸርነት ጉግሳን በአዲስ ግደይ ፣ ቢኒያም በላይን በቢኒያም ፍቅሬ ሲተኩ ታንዛኒያዎች ኔክሰን ክሌመንትን በፓስካል ጋውዴንስ ከተኩ በኋላ ጨዋታው ሲቀጥል በፈጣን ሽግግር ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል ያመሩት ታንዛኒያዎች አደገኛ ሙከራን አድርገዋል። በግራ ተቀይሮ የገባው ፓስካል ጋውዴንስ ያሻማውን ኳስ ክሌመንት ፍራንሲስ በግንባር ገጭቶ የግቡ አግዳሚ ሲመልሰው ሰይድ ሀብታሙ የተመለሰችውን ኳስ ይዟታል።

መስመሮችን በይበልጥ የማጥቃት ምንጫቸው በማድረግ ወደ ሳጥን የሚጣሉ ተሻጋሪ ኳሶችን እየተጠቀሙ ጫና መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረጉት ታንዛኒያዎች በሌላ ሙከራቸው ከማዕዘን ኢድዊን ቻርለስ አሻምቶ ኢብራሂም አብዱላ ገጭቶ ኳሷ በግቡ ቋሚ በኩል ታካ ወጥታለች። ከቀዳሚው አጋማሽ አኳያ ወረድ ባሉ አቀራረቦች የተገኙት ዋልያዎቹ በቅብብል ያደረጉ የነበሩትን አጨዋወት በዚህኛው አጋማሽ ለመድገም እንቅስቃሴዎችን ቢያዘወትሩም ለስህተት ቅርብ መሆናቸው በቀላሉ ኳሶቻቸው ለተጋጣሚያቸው ሲሳዮች ሲሆኑ ተንፀባርቋል።

ተጨማሪ የተጫዋች ቅያሪዎችን አድርገው አንዳች ነገርን ፈጥሮ ለመውጣት በድግግሞሽ ከማጥቃት ያልቦዘኑት የታይፋ ኮከቦቹ ከተሻጋሪ የመጣን ኳስ ኢድዊን አስቆጠረው ሲባል በረከት ተደርቦ ያወጣበት እና ከቅጣት ምት ኖቫተስ ዲስማስ መቶ ሰይድ ሀብታሙ በእቅፉ የተቆጣጠራት የተደረጉ አደገኛ ሙከራዎቻቸው ሆነዋል። አልፎ አልፎ የሚያገኟቸውን ጥቂት ዕድሎች በዝንጉነት ሲያመክኑ የታዩት ዋልያዎቹ 87ኛው ደቂቃ ላይ በሰማያዊ ለባሾቹ ሌላ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው በመልሶ ማጥቃት መነሻን ያደረገች ኳስን ከሳጥን ውጪ ተቀይሮ የገባው ሙዳተሪ ያህያ አክርሮ መቶ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ኳሷ ታካ ከወጣች በኋላ ጨዋታውም ጎል ሳያስመለክተን 0ለ0 ተደምድሟል።