አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ከጨዋታው በኋላ ምን አሉ?

“በእኔ እይታ አቻ ይገባናል” አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌበ2025 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በማጣርያው የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ከታንዛኒያ ጋር አድርገው ያለግብ የተለያዩት ዋልያዎቹ አሰልጣኝ የሆኑት ገብረመድኅን ኃይሌ ከጨዋታው በኋላ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው…

ጨዋታው ጠንካራ ነበር። ጨዋታውን ለማሸነፍ ሞክረናል። ግን ሳይሳካልን አቻ ወተናል። በእኔ እይታ አቻ ይገባናል። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ተጫውተን ነበር። በሁለተኛውን አጋማሽ ደግሞ ታንዛኒያዎች የተሻሉ ነበሩ። በአጠቃላይ ግን አቻ ለሁለታችንም ምንም ማለት አይደለም።

ስለተጋጣሚ ቡድን…

የተጋጣሚ ቡድን ጠንካራ ቡድን ነው። በሜዳቸው ነው የተጫወቱት። ጥሩ ደጋፊም ነበራቸው። በሚያውቁት ሜዳም ነው የተጫወቱት። የዐየር ፀባዩንም ይጠቀማሉ። እኛ እንግዳ ነን። ቡድኑ የአጨራረስ ችግር አለበት። ግን እያደገ የሚሄድ ቡድን ነው።ስለ አጥቂ መስመር…

እኛም ከአጨራረስ ጋር ተያይዞ ችግሮች አሉብን። በቡድን አጨዋወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ረገድ ብዙ ችግር የለብንም። በቡድናችን ውስጥ ጥሩ “9” ቁጥር የለም። ይህ ቢሆንም ግን እንደ ቡድን ለመጫወት ሞክረናል። በ”9″ ቁጥር አጥቂ ከመጫወት ይልቅም በሀሰተኛ “9” ቁጥር ለመጫወት ሞክረናል። ይሄንን የአጥቂ ችግር እናውቀዋለን። ለዛም ነው ሀሰተኛ “9” ቁጥር የተጠቀምነው። ስናደርግ የነበረው ኳሱን በአግባቡ ተቆጣጥረን ወደ ተጋጣሚ ቡድን በጋራ ለመሄድ ስንጥር ነበር። ይህ እንደ ሀገርም ያለብን ችግር ነው። ይሄንን ነገር ለመቅረፍ እየሰራን ነው። በጊዜ ሂደት መቀረፉ አይቀርም።