የ2016 የፕሪምየር ሊጉ ኮከቦች ሽልማት መቼ ይደረጋል ?

ከቀደሙት ዓመታት አንፃር በተለየ መዘግየት ያሳየው የ2016 የዓመቱ ኮከቦች የሽልማት መርሃግብር መች ይካሄዳል ስትል ሶከር ኢትዮጵያ ማጣራት አድርጋለች።


የሊጉ የአክሲዮን ማኅበር የፕሪምየር ሊጉን ውድድር በበላይነት መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዓመቱ መጠናቀቂያ ላይ የዓመቱ የፕሪምየር ሊጉን ኮከቦች እንደሚሸልም ይታወቃል ዘንድሮ ግን ከወትሮው በተለየ የዚህ የሽልማት መርሃግብር መዘግየት የሽልማቱንም ለዛ አደብዝዞታል።

ይህን ተከትሎ የሽልማቱ መርሃግብር የዘገየበትን ምክንያት እና መቼ እንደሚካሄድ የጠየቅናቸው የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ሲናገሩ“ መዘግየቱ እንዳለ ሆኖ ከተደራራቢ የስራ ሁኔታዎች የተነሳ ፕሮግራሙን ለማድረግ ዘግይተናል።” ያሉ ሲሆን አያይዘውም የ2017 የውድድር ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ መርሃግብሩ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረጉ እንደሆነ ገልፀውልናል።

ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የሽልማት መርሃግብሩን ሁሉንም ተሳታፊ አካላት በሚገኙበት ድሬዳዋ ከተማ ላይ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ጥረቱ የማይሳካ ከሆነ በአዲስ አበባ እንደሚደረግ ለማወቅ ችለናል።