ዲሲ ፓወር ኢትዮጵያዊቷን አጥቂ ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል።
ከወራት በፊት ለተከታታይ ሦስት ዓመት ቻምፒዮን የሆነችበትን ክለቧን ንግድ ባንክን ለቃ ለቨርጂኒያ ማራውደርስ ፊርማዋን በማኖር በአሜሪካ ፕሮፌሽናል ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የተጫወተች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች መሆን የቻለችው ሎዛ አበራ አሁን ደግሞ ማረፊያዋ በሱፐር ሊጉ የሚሳተፈው ዲሲ ፓወር ሆኗል።
ለብሔራዊ ቡድን ባደረገቻቸው 31 ጨዋታዎች 39 ጎሎችን ያስቆጠረችው ሎዛ በ2016 አጋማሽ ቨርጂኒያ ማራውደርስን ከተቀላቀለች በኋላ ደግሞ በቋሚነት በጀመረችባቸው 8 ጨዋታዎች 9 ጎሎችን ማስቆጠር ችላለች።
በትናንትናው ዕለት አጥቂዋን ወደ ስብስቡ መቀላቀሉን ይፋ ያደረገው የዲሲ ፓወር እግርኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ የሆኑት ፍሬደሪክ ብሪላንት “ሎዛ አበራን ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ወደ ስብስባችን በመቀላቀላችን ደስ ብሎናል። የግቡን መረብ በተደጋጋሚ ማግኘት ትችላለች ፤ ለቡድናችንም ጥሩ አቀባበል ትሆናለች።” ሲሉ የተደመጡ ሲሆን የክለቡ ፕሬዚዳንት ጆርዳን ስቱዋርት በበኩላቸው “ሎዛ በአጥቂ ሥፍራ ላይ ፈጣሪ እና ጎል አሽታች የሆነች እጅግ ጎበዝ ተጫዋች ስትሆን ሀገሯን በመምራት በዓለም መድረክ በአፍሪካ እግርኳስ ግንባር ቀደም መሆኗን ዐሳይታለች። DMV በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን መኖሪያ በመሆኑ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቿን ማስፈረማችን ዲሲ ፓወር በአካባቢው እና በሌሎችም የኢትዮጵያ ደጋፊዎች ዘንድ እንዲወደድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።” ብለዋል።
የአሜሪካ ሴቶች ሱፐር ሊግ ነሐሴ 11 2016 የተጀመረ ሲሆን ዲሲ ፓወር እግርኳስ ክለብ በሜዳው የሚያደርገውን የመጀመሪያ ጨዋታ መስከረም 3 2017 ከፎርት ላውደርዴል ጋር በኦዲ ፊልድ ያከናውናል።