ጀርመን ለትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ጥሪ አደረገች

ሁለት ተስፈኛ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የወቅቱን የዓለም ቻምፒዮን ሊወክሉ ነው።

የጀርመን ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከቀናት በኋላ ከሜክሲኮ ጋር ላለበት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በመርሐግብሩ የሚሳተፉ ተጫዋቾች ይፋ ሲያደርግ በዝርዝሩ ውስጥ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ተካትተዋል። የጀርመን ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን ለመወከል ጥሪ የቀረበላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባየር ሊቨርኩሰን ታዳጊ ቡድን የሚጫወተው ነቤ ሲራክ ዶሚኒክ እና በኢንትራክት ፍራንክፈርት ታዳጊ ቡድን የሚጫወተው ናትናኤል አብርሃ ናቸው። በ ‘DFB’ የወጣቶች ሊግ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ሁለቱም ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ የሚጫወቱ ሲሆን በቅዳሜው ጨዋታ ለቋሚነት እርስ በእርስ ይፎካከራሉ።

በ2022 አሳዳጊ ክለቡን ቪክቶርያ ኮሎኝ በመልቀቅ ላለፉት ዓመታት በባየር ሊቨርኩሰን ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድን በመጫወት ላይ የሚገኘው የአስራ አምስት ዓመቱ ነቤ ሲራክ በጥቂት ጊዜያት ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት ላይ የሚገኝ ተጫዋች ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ለጀርመን ከአስራ አምስት እና አስራ ስድስት ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ዘጠኝ ጨዋታዎች ማድረግ የቻለው ይህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሁን ደግሞ ከአንድ ዓመት በፊት የዓለም ዋንጫ እና የአውሮፓ ዋንጫ ያሸነፈው እና በዕድሜ እርከኑ ከጠንካራ ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰውን  የጀርመን ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለማገልገል ጥሪ ደርሶታል።

ሌላው ጥሪ የተደረገለት ተጫዋች በኢንትራክት ፍራንክፈርት ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድን ውስጥ እየተጫወተ የሚገኘው የአስራ ስድስት ዓመቱ የቀኝ መስመር ተከላካይ ናትናኤል አብርሃ በዘንድሮው ውድድር ክስተት ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል። በቅርቡ በጀመረው እና አራተኛ ሳምንቱ ላይ ባስቆጠረው የታዳጊዎች ሊግ ‘U17 Nachwuchsliga’ ላይ በአራት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች አስቆጥሮ አንድ ግብ የሆነ ኳስ በማመቻቸው ዓመቱን በግሩም ሁኔታ የጀመረው ይህ ተስፈኛ ከዚህ ቀደም ለጀርመን ከአስራ ስድስት ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ስምንት ጨዋታዎች ማድረግ የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ አንድ እርከን ከፍ ብሎ ጀርመንን እንዲያገለግል ጥሪ ቀርቦለታል።

ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ከ2016 ጀምሮ በኑረንበርግ ወጣት ቡድኖች ቆይታ ያለው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኪሩቤል ታዬ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድን ወደ ከአስራ ዘጠኝ ዓመት በታች ቡድን አድጓል።