በዋልያዎቹ የዛሬ ልምምድ አንድ ተጫዋች አልሠራም

 

ሁለተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታውን ሰኞ በሚያደርገው የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውስጥ አንድ ተጫዋች ልምምድ አለመሥራቱ ተሰምቷል።

የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታውን ለማድረግ ዳሬ ሰላም የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ረቡዕ ከታንዛኒያ አቻው ጋር ያደረገውን ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ይታወቃል። ዋልያዎቹ ከታንዛኒያ ጨዋታ በኋላ የፊታችን ሰኞ ጳጉሜ 4 ቀን ከኮንጎ ዲ.ሪ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ ትናንት እና ዛሬ መደበኛ ልምምዳቸውን በኬኤምሲ ስታዲየም አከናውነዋል።

በዛሬው ልምምድ ላይ አማካዩ ወገኔ ገዛኸኝ በመጠነኛ ጉዳት ምክንያት ልምምድ አለመሥራቱን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ አመላክቷል። ወገኔ በታንዛኒያው ጨዋታ ላይ ተጎድቶ ተቀይሮ የወጣ መሆኑ ሲታወቅ ዛሬ ልምምድ አለመሥራቱን ተከትሎ ለቀጣይ ጨዋታ ይደርሳል ወይስ አይደርስም የሚለውን ለማወቅ በነገው የመጨረሻው ልምምድ ላይ ታይቶ የሚወሰን መሆኑን ሰምተናል።

የተቀሩት የቡድኑ አባላት በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን የፊታችን ሰኞ ዋልያዎቹ ከኮንጎ ዲ.ሪ ጋር ፍልሚያቸውን ምሽት አራት ሰዓት ላይ የሚያደርጉ ይሆናል።