ከፍተኛ ሊግ | ሶሎዳ ዓድዋ ዋና እና ምክትል አሰልጣኝ ቀጥሯል

ሶሎዳ ዓድዋዎች ከዓመታት በኋላ ወደ ሀገራዊ ውድድሮች ለመመለስ ዝግጅት ጀምረዋል።

ከዓመታት በኋላ ወደ እንቅስቃሴ ተመልሰው በተጠናቀቀው ዓመት በትግራይ ዋንጫ በመሳተፍ ላይ የቆዩት እና በቀጣይ ውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ የሚገኙት ሶሎዳ ዓድዋዎች አሰልጣኝ አሸናፊ አማረን ዋና አሰልጣኝ አድርገው ሲሾሙ ሐዱሽ አወጣኸኝን በምክትልነት ቀጥረዋል።

ከዚህ ቀደም በወልዋሎ በሥራ አስኪያጅነት ከዛ በፊትም ከ2007 ጀምሮ ትግራይን እየመራ በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በዋና አሰልጣኝነት የሠራው እና በመቐለ ከተማ በተለያዩ የታዳጊ ቡድኖች ማሰልጠን የቻለው ወጣቱ አሰልጣኝ አሁን ደግሞ በከፍተኛ ሊጉ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ለሚገኙት ሶሎዳ ዓድዋዎች ለማሰልጠን ተስማምቶ ከቀናት በፊት በይፋ ሥራውን ጀምሯል።

የአሸናፊ አማረ ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ በዛሬው ዕለት የተሾመው ደግሞ ሐዱሽ አወጣኸኝ ነው። በተጫዋችነት ሕይወቱ ለአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ፣ ጉና ንግድ፣ መቻል፣ መቐለ 70 እንደርታ እና አክሱም ከተማ መጫወት የቻለው የቀድሞው የአማካይ ተከላካይ አሁን ደግሞ ወደ ማሰልጠኑ በመግባት የሶሎዳ ዓድዋ ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ ለመስራት ፊርማውን አኑሯል።

ከቀናት በፊት ነባር ተጫዋቾች በመያዝ ልምምድ የጀመሩት ዓድዋዎች በቀጣይ ሳምንታት አዳዲስ ተጫዋቾች ለማስፈረም በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል።