በዋልያዎቹ ስብስብ ተጨማሪ ተጫዋቾች ጉዳት አስተናግደዋል

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በሚመራው የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ ከሰኞው ተጠባቂ ጨዋታ አስቀድሞ አዳዲስ የጉዳት ዜናዎች ተሰምተዋል።

ሰኞ አመሻሻሽ በዳሬሰላም ከዲ.አር ኮንጎ አቻቸው ጋር ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ ጨዋታ የሚያደርጉት ዋልያዎቹ ዛሬም መደበኛ ልምምዳቸውን እየከወኑ ባለበት ተጨማሪ የተጫዋቾች ጉዳት ስለማስተናገዳቸው ሶከር ኢትዮጵያ ከስፍራው መረጃ አግኝታለች።

በቁርጭምጭሚት ጉዳት ምክንያት ትናንት ከቡድኑ ጋር ልምምድ ያልሰራው ወገኔ ገዛኸኝ ዛሬ ቀለል ያለ ልምምድ መጀመሩ ሲታወቅ በዛሬው የልምምድ መርሃግብር ደግሞ አጥቂው ቢንያም ፍቅሬ እና አማካዩ አብነት ደምሴ ተጨማሪ ጉዳት ያስተናገዱ ተጫዋቾች ሆነዋል።

ቢንያም ፍቅሬ በልምምዱ መገባደጃ ላይ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት አለመጨረሱ ሲሰማ አብነት ደምሴ ደግሞ ባጋጠው ህመም በዛሬው ልምምድ ላይ አለመሳተፉን ሰምተናል።

ወገኔ ገዛኸኝ ለቀጣይ ጨዋታ የመድረሱ ነገር ነገ በመጨረሻው ልምምድ ላይ እንደሚታወቅ ሲጠበቅ ቢንያም ፍቅሬ እና አብነት ደምሴ ለሰኞው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገር ግን አጠራጣሪ ሆኗል።