ነገ በታንዛኒያ የሚደረገውን የኢትዮጵያ እና ኮንጎ ዲ.አር ጨዋታ የሰሜን አፍሪካ አልቢትሮች ይመሩታል።
በሞሮኮ አዘጋጅነት በሚከናወነው የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የአህጉራችን ሀገራት በተለያዩ ምድቦች ተቦድነው የማጣሪያ ጨዋታቸውን ካለንበት ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ማድረግ የጀመሩ ሲሆን የምድብ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ደግሞ ከነገ ጀምሮ ያከናውናሉ።
በምድብ 8 ከታንዛኒያ፣ ኮንጎ ዲ.አር እና ጊኒ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ረቡዕ ከሜዳው ውጪ ታንዛኒያን ገጥሞ ነጥብ የተጋራ ሲሆን በደጋፊው ፊት ማከናወን የነበረበትን የነገ ጨዋታ እዛው ታንዛኒያ ላይ በገለልተኛ ሜዳ ለማድረግ እየተዘጋጀ ይገኛል።
ነገ ምሽት 4 ሰዓት የሚደረገውን ጨዋታ ካፍ ቀደም ብሎ ከዋና እና አራተኛ ዳኛው ውጪ የቱኒዚያ እና ሊቢያ ረዳት አልቢትሮች እንዲመሩ ምደባ አርጎ የነበረ ሲሆን አሁን ግን አራቱም ዳኞች ከሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጄሪያ እንዲሆኑ መደረጉ ታውቋል።
በዚህም ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ላህሉ ቤንብራሃም፣ በረዳትነት አቤስ አክራም ዜርሁኒ እና ሀምዛ ቡዚት በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ነቢል ቡኻልፋ እንደሚመሩት ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ የዋልያዎቹ የነገ ተጋጣሚ ኮንጎ ዲ.አር በሦስት ነጥብ ስትመራ ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ በእኩል አንድ ነጥብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ጊኒ ደግሞ ያለ ምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።