ባህር ዳር ከተማ የቀድሞ ተጫዋቾቹን አስፈርሟል

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ የሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ዝውውር ቋጭቷል።

በአዳማ ከተማ መቀመጫቸውን በማድረግ ለ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየሠሩ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርካታ የቀድሞ ተጫዋቾቻቸውን ወደ ቡድናቸው እየቀላቀሉ የሚገኙ ሲሆን አሁን ደግሞ በክለቡ የተስፋ ቡድን ውስጥ ከዚህ ቀደም የተጫወቱ ሁለት ተጫዋቾችን የግላቸው አድርገዋል።

ክንዱ ባየልኝ የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ሆኗል። በተከላካይ ቦታ ላይ ከባህር ዳር ተስፋ ቡድን በኋላ በኮልፌ ቀራኒዮ ፣ አውስኮድ እና ባለፈው ዓመት በባቱ ከተማ የከፍተኛ ሊግ ቆይታን አድርጎ ነው ወደ ጣና ሞገዶቹ ቤት ያመራው።

ሌላኛው ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች የመስመር አጥቂው ኪዳነማርያም ተስፋዬ ሲሆን ከባህር ዳር ተስፋ እና ዋና ቡድን በኋላ ከስልጤ ወራቤ ጋር በከፍተኛ ሊጉ ግልጋሎት ሰጥቶ ወደ ቀድሞው ቡድኑ ተመልሷል።