ኢትዮጵያ መድን ሁለት ወጣት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ሁለት ተጫዋቾች ከኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ መድንን በሦስት ዓመት ውል ተቀላቅለዋል።

በአዳማ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሲሠሩ ቆይተው በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ እየተካፈሉ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች በለቀቋቸው በርካታ ተጫዋቾች ምትክ አዳዲስ ተጫዋቾችን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወደ ስብስባቸው መቀላቀል የቻሉ ሲሆን አሁን ደግሞ ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ቡድኑ ሁለት ወጣት ተጫዋቾችን ከኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ በሦስት ዓመት ውል አስፈርሟል።

የቀኝ መስመር ተከላካዩ በረከት ካሌብ የመድን አዲሱ ፈራሚ ሆኗል። ወጣቱ ተጫዋች ከሀዋሳ ከተማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ጋር ከተለያየ በኋላ በተመሳሳይ የዕድሜ ዕርከን ቡድን ወዳለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በማምራት የተጫወተ ሲሆን ላለፉት ሁለት ዓመታትም በንግድ ባንክ ከ20 ዓመት በታች ስብስብ ውስጥ አስደናቂ እንቅስቃሴን ከማድረግ በተጨማሪ በአምበልነትም ጭምር ቡድኑን መርቷል።

ሌላኛው የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌን ቡድን የተቀላቀለው አማካዩ ብሩክ በላቸው ነው። በወላይታ ድቻ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ድንቅ ጊዜን ያሳለፈው ይህ ተጫዋች ከድቻ ጋር ያለውን ውል በስምምነት አቋርጦ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ክለብ አምርቷል።