ከሽንፈቱ በኋላ የዋልያዎቹ አለቃ ምን አሉ?

“በሁለት ጨዋታዎች ግብ አላስቆጠርንም ማለት በሦስተኛው እና አራተኛው ጨዋታ ግብ አናገባም ማለት አይደለም” ገብረመድህን ኃይሌ


ስለጨዋታው…

በጨዋታው ተሸንፈናል። ተጋጣሚያችን ጠንካራ ቡድን ነው። ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረናል። በዚህም በርካታ የግብ ማግባት ዕድሎችን ፈጥረናል። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ሦስት እና አራት ሙከራዎችን አድርገናል። ነገር ግን ዕድሎቹን መጨረስ አልቻልንም። ከዚህ መነሻነት በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩብን ሁለት ጎሎች ተሸንፈናል። በአጠቃላይ ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። ለእኛ ሽንፈት ጥሩ አይደለም ግን በቀጣይ እናስተካክላለን።

ስለሽንፈቱ ምክንያት…

ተጋጣሚያችን ኮንጎ ዲ.አር ቀላል ተጋጣሚ አልነበረም። በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነውን ነበር። የተከላካይ መስመራችንም የትኩረት ማነስ አጋጥሞት ነበር። ዛሬ እንደባለፈው ጨዋታ የተከላካይ መስመራችን ጥሩ አልነበረም። በዚህም መነሻነት በቀላሉ ግቦችን አስተናግደናል። ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው።

ግብ ሳያስቆጥሩ ስለመውጣታቸው…

ያጋጥማል። በሁለት ጨዋታዎች ግብ አላስቆጠርንም ማለት በሦስተኛው እና አራተኛው ጨዋታ ግብ አናገባም ማለት አይደለም። ግብ ማግባት እንችላለን። ችግራችንን አይተናል። በችግራችን ላይ ደግሞ በደንብ እንሰራለን።