ጎፈሬ ከዩጋንዳው ክለብ ዩፒፒሲ ጋር ስምምነት ፈፀመ

ኢትዮጵያዊው የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ የዩጋንዳ የህትመት ተቋም ክለብ ከሆነው ዩፒፒሲ ጋር የሦስት ዓመት የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ተፈራረመ።

ለስኬት ያበቁትን ሰራተኞቹን ለማበረታታት እና የስምምነቱ የጀርባ አጥንት እንደሆኑ ለማሳየት በተቋም የማምረቻ ስፍራ በተደረገው ስምምነት ላይ የጎፈሬ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን እንዲሁም የዩፒፒሲ ክለብ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ኦፒዮ ተገኝተዋል። በቅድሚያ ንግግር ያደረጉት አቶ ሳሙኤል መኮንን መላው ኢትዮጵያዊያንን እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ ካሉ በኋላ ለተቋሙ ስኬታማ ከነበረው የ2016 የማገባደጃ ቀን ላይ ሌላ አዲስ ስምምነት በመፈፀማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ከዩፒፒሲ ጋር ያደረጉት ስምምነት ለሦስት ዓመታት እንደሚዘልቅ በመጠቆም ክለቡ ከሚጠቀምባቸው አስፈላጊ ትጥቆች በተጨማሪ በየዓመቱ እስከ አስር ሺ የደጋፊ መለያዎችን እንደሚቀርቡ አብራርተዋል። አቶ ሳሙኤል ጨምረውም ኢትዮጵያዊያን በ2017 ዓመት በአዳዲስ ነገሮች ጎፈሬን እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አዲሱ የዩፒፒሲ ፕሬዝዳንት ሚስተር ኦፒዮ በበኩላቸው ክለቡ በአዲስ ባለቤቶች ከተያዘ በኋላ ስለጎፈሬ ያለው አቀባበል መልካም እንደሆነ አመላክተው የጎፈሬ የምርት ጥራት ከሌሎች ጋር ከመወዳደርም አልፎ እንደሚበልጥ በመመስከር ተቋማቸው ከጎፈሬ ጋር በፈፀመው ስምምነት ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል።


በሦስት ዓመቱ ስምምነት ጎፈሬ ለቡድኑ ከመጫዎቻ ጀምሮ እስከ መለማመጃ ድረስ አስፈላጊ ትጥቆችን ጨምሮ የደጋፊዎች መለያዎችን በስፖንሰርሺፕ እና በግዢ እንደሚያቀርብ ተመላክቷል።


በስምምነቱ ፍፃሜ አቶ ሳሙኤል የኢትዮጵያን የዘመን መለወጫ ተከትሎ የጎፈሬን ስጦታ ለክለቡ ፕሬዝዳንት የሰጡ ሲሆን ሚስተር ኦፒዮም ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው መላው ኢትዮጵያዊያንን እንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።