የንግድ ባንክ የመልስ ጨዋታ ዛንዚባር ላይ ይከናወናል

ያንግ አፍሪካንስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በታንዛኒያ ርዕሰ መዲና ዳሬ ሰላም ሳይሆን በዛንዚባር አማኒ እንደሚያስተናግድ ታውቋል።

የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ የሚደረጉ ሲሆን የሀገራችን ተወካይ ክለብ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዙሩ የምስራቅ አፍሪካ ኃያል ክለብ የሆነውን ያንግ አፍሪካንስ ለመግጠም እየተዘጋጀ ይገኛል። የሁለቱ ቡድኖች የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ከፊታችን በሚመጡት ተከታታይ ቅዳሜዎች የሚከናወኑ ሲሆን የታንዛኒያው ክለብ ያንጋ በሜዳው በክለቡ መቀመጫ ከተማ ማድረግ የሚችለውን ጨዋታ ወደ ዛንዚባር እንደወሰደው ታውቋል።

በታንዛኒያ በበርካቶች ዘንድ ከሚደገፉት ሁለት አውራ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ያንጋ በዋና ከተማው ዳሬሰላም ማድረግ የሚችለውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ወደ ዛንዚባሩ አማን ኮምፕሌክስ ስታዲየም ወስዶታል።

በቻይና መንግስት እርዳታ በ1970 የተገነባው እና ዓምና እድሳት ተደርጎለት እንደ አዲስ የተመረቀው 15 ሺ ተመልካቾችን መያዝ የሚችለው አማን ኮምፕሌክስ ስታዲየም የተፈጥሮ ሳር ሜዳ ያለው ሲሆን ያንጋ በርካታ ደጋፊዎች ከሚገኙበት ዳሬሰላም ከሚገኘው ዋናው የመጫዎቻ ስታዲየም (ቤንጃሚን ምካፓ) ወደ ዛንዚባር ጨዋታውን መውሰዱ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጫናዎችን እንደሚቀንስ ይጠበቃል።

አዘውትሮ በዚህ ስታዲየም የማይጫወተው ያንጋ ለመጨረሻ ጊዜ በስታዲየሙ ጨዋታ ያረገው ግንቦት 25 በሲአርዲቢ ፌዴሬሽን ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ ከአዛም ጋር ሲሆን የውድድሩን ዋንጫም በዕለቱ ከፍ ማድረጉ አይዘነጋም።

ለዚህ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዲስ አበባ በቀጥታ ወደ ዛንዚባር በዐየር ትራንስፖርት የሚበር ሲሆን ምናልባት ያንጋ እና ተጓዥ ደጋፊዎች ለ1:30 የሚፈጅ የባህር ላይ ጉዞ በማድረግ ጨዋታውን ዛንዚባር ላይ እንደሚከውኑ ይጠበቃል።

በተያያዘ ዜና የፊታችን ቅዳሜ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ያንግ አፍሪካንስ 25 ተጫዋቾችን በመያዝ ረፋድ ላይ አዲስ አበባ መግባታቸው ተሰምቷል።