የአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬው መቐለ 70 እንደርታ ጋናዊ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች በአንድ ዓመት ውል የግሉ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቀናት በኋላ ጅምሩን ሲያደርግ መቐለ 70 እንደርታ በሊጉ ላይ ተሳታፊ ይሆናል። በአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ መሪነት በክለቡ መቀመጫ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን አገባዶ በአሁኑ ሰዓት በሀዋሳ ከተማ ለወዳጅነት ጨዋታ የከተመው ቡድኑ ከላይቤሪያዊው ግብ ጠባቂ አልፋኖ ሴሳይ እና ከጋናዊው ተከላካይ ሸሪፍ መሐመድ በመቀጠል ቡድኑ የ30 ዓመቱን ጋናዊ አጥቂ ኮፊ ኮርድዚ ሦስተኛው የውጪ ዜጋ ፈራሚው አድርጓል።
አንድ ሜትር ከሰማንያ አምስት ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ተጫዋቹ በሁለት አጋጣሚዎች ለሀገሩ ኸርትስ ኦፍ ኦክ መጫወት የቻለ ሲሆን በመቀጠል በኳታር ሁለተኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊ ክለብ ሙ አይተር እንዲሁም ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለሌጎን ሲቲ እና እንዲሁም የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ ለሊቢያው አሊተሀድ ቤንጋዚ በ26 ጨዋታዎች ተሰልፎ 5 ግቦች በማስቆጠር ከቋጨ በኋላ ቀጣዩ መደረሻው የምዓም አናብስቱ ቤት ሆኗል።