ፈረሰኞቹ የታዳጊ ቡድን ፍሬያቸውን ዳግም ለማስፈረም ተስማምተዋል

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚሰለጥኑት ፈረሰኞቹ ወጣቱን አጥቂ ለማስፈረም ተስማምተዋል።

ለሸገር ደርቢ ጨዋታ ወደ ሀገረ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ አምርተው የተመለሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ድሬዳዋ ከማቅናታቸው አስቀድመው ተጨማሪ ዝግጅታቸውን ዛሬ በቢሾፍቱ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ የጀመሩ ሲሆን አሁን ደግሞ ወጣቱን አጥቂ ለማስፈረም መስማማታቸውን አውቀናል።

ለፈረሰኞቹ ለመጫወት የተስማማው ፉአድ አብደላ ነው። ከክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ውድድር ጀምሮ ከታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ደርሶ ለክለቡ እስከ 2015 ድረስ ግልጋሎት የሰጠው ፉአድ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ቆይታ ማድረጉ ሲታወቅ አሁን ደግሞ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ አሳዳጊው ክለብ መመለሱ እርግጥ ሆኗል።

ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ፉአድ የህክምና ምርመራውን በማድረግ ፊርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል።