የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚወዳደረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲቋጭ የዘጠኝ ነባሮችን ውል ደግሞ አራዝሟል።

በ2016 የውድድር ዘመን በሰበሰባቸው 56 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ማጠናቀቅ የቻለው የአሰልጣኝ መሠረት ማኔው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለ2017 የሊግ ተሳትፎው በለቀቁ በርካታ ተጫዋቾች ምትክ ሊሆኑ የሚችሉ አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የዘጠኝ ነባሮችን ውል ደግሞ አድሷል።

ቡድኑ ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች ስንመለከት ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እና ያለፈውን ዓመት ከሲዳማ ቡና ጋር ያሳለፈችው አጥቂዋ ማህሌት ምትኩ ፣ በአዲስ አበባ እና በሀዋሳ ቆይታ የነበራት የመስመር ተጫዋቿ በሻዱ ረጋሳ ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ላለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ የነበረችው አጥቂዋ እየሩስ ወንድሙ ፣ ከወላይታ ድቻ ከተገኘች በኋላ በጌዲዮ ዲላ እንዲሁም ከመቻል ጋር ረዘም ያሉ ዓመታት ያሳለፈችው ተከላካዩዋ ቤተልሔም በቀለ በባህር ዳር እና አዳማ የምናውቃት የመስመር አጥቂዋ ሳባ ኃይለሚካኤል ፣ የልደታ ክፍለ ከተማዋ አጥቂ ህዳት ካሱ ፣ በባህር ዳር እና ድሬዳዋ ቆይታ ያደረገችው አጥቂዋ ሊዲያ ጌትነትን ጨምሮ ብርሃን ኃይለሥላሴ አጥቂ ከሀምበርቾ ፣ ትዝታ ኃይለማርያም ተከላካይ ከአርባምንጭ ፣ ሃና ሲሳይ አማካይ ከአርባምንጭ ፣ ሰርካዲስ ካሳዬ አማካይ ከአርባምንጭ እና ባንቺ ይርጋ ተስፋዬ ተከላካይ ከአርባምንጭ ከተማ ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ቡድኑ ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ የነባሮቹን ተጫዋቾች ማለትም የግብ ጠባቂዎቹን ማርታ በቀለ ፣ እየሩሳሌም ሎራቶ እና ምህረት ተሰማን ፣ የተከላካዮቹ እፀገነት ብዙነህ እና መስከረም ካንኮ የአማካዮቹ ዙፋን ደፈርሻ ፣ ንግስት ኃይሉ እና ንግሥት አስረስ እንዲሁም የአጥቂዋን ፀጋነሽ ወራናን ኮንትራት አድሷል።