በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት የሚደረገው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የክለቦች እና ክልሎች ሻምፒዮና በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ በተደረገ አንድ ጨዋታ ጅማሮውን አድርጓል።
ከውድድሩ አስቀድሞ በትናንትናው ዕለት በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል በተካሄደው የዕጣ ማውጣት ስነስርዓት ስምንት ቡድኖች በሁለት ምድብ ሲደለደሉ ፤ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ባህርዳር ከተማ ፣ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምድብ ‘ሀ’ ሲመደቡ ሀዋሳ ከተማ ፣ሲዳማ ክልል፣ ወላይታ ዲቻ እና አርባምንጭ ከተማ በምድብ ”ለ” መደልደላቸው ይታወሳል።
ዛሬ በተከናወነው የመክፈቻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲያገናኝ ከጨዋታው ጅማሮ አስቀድሞም የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አንበሴ አበበን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ውድድሩን አስጀምረዋል።
ተመጣጣኝ ፉክክር በተደረገበት በዚሁ የመክፈቻ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ሳይሸናነፉ ጨዋታቸውን ያለ ግብ በአቻ ውጤት ፈፅመዋል።
ወድድሩ ነገም ቀጥሎ ሲውል በምድብ “ሀ” ባህርዳር ከተማ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጨዋታ ረፋድ 3 ሰዓት ሲደረግ በምድብ “ለ” ሀዋሳ ከተማ ከወላይታ ዲቻ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ 5 ሰዓት ላይ ይደረጋል። ዛሬ ጅማሮውን ያደረገው ውድድሩ እስከ መስከረም 16 ድረስ እንደሚቆይም ታውቋል።