በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር ቅድመ ማጣርያ የመጀመሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሜዳው በያንግ አፍሪካንስ 1ለ0 ተሸንፏል።
በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር ቅድመ ማጣርያ የዩጋንዳውን ኤስ ሲ ቪላ በድምር ውጤት 3ለ2 አሸንፎ የመጣው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለተኛው ዙር ቅድመ ማጣርያ ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር ተገናኝቶ የመጀመሪያውን ጨዋታ በሜዳው ሲያስተናግድ ከባለፈው አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ገብቷል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ የነበራቸው ያንግ አፍሪካንስ ገና በ3ኛው ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ፕሪንስ ምፑሜሌሎ ዱቤ ከረጅም ርቀት በተጣለለት ኳስ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አስወጥቶበታል።
ግብ ከማስተናገድ በተረፉበት ቅጽበት በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የደረሱት ንግድ ባንኮች በአዲስ ግደይ ያደረጉት ሙከራ በተከላካይ ተደርቦ ሲመለስባቸው ያንኑ ኳስ ከሳጥን ውጪ ቢኒያም ካሳሁን መትቶት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ይዞበታል።
በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በጥቂት ንክኪዎች በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት ያንግ አፍሪካንስ 13ኛው ደቂቃ ላይ ያለቀለት የግብ ዕድል ፈጥረው ፓኮሜ ፒኦዶህ ዙዟ በቀኝ መስመር በድንቅ ሁኔታ እየገፋ የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ አሻግሮት ፕሪንስ ምፑሜሌሎ ዱቤ ነጻ ሆኖ ቢያገኘውም ያደረገው ሙከራ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ በርካታ ቅብብሎችን በማድረግ ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማጥቃት ሲሞክሩ በዚሁ እንቅስቃሴያቸው ስህተት ሠርተው 41ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊቆጠርባቸው ነበር ፤ ሆኖም ፕሪንስ ምፑሜሌሎ ዱቤ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ፍሬው ጌታሁን በአስደናቂ ሁኔታ አግዶበታል።
ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ በተጨመረው አንድ ደቂቃ ውስጥ ያንግ አፍሪካንስ ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ ተሳክቶላቸው በፕሪንስ ምፑሜሌሎ ዱቤ ግሩም ጎል 1ለ0 እየመሩ ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ግለት በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 58ኛው ደቂቃ ላይ ያንግ አፍሪካዎች ግብ ማስቆጠር የሚችሉበት አጋጣሚ ፈጥረው ከግራ መስመር የተነሳውን ኳስ ብቻውን ያገኘው ማክሲ ምፒያ ንዜንገሊ ተረጋግቶ በኃይል በመምታት ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
አልፎ አልፎ የታንዛኒያ ተወካዮች ከሚፈጥሯቸው የግብ ዕድሎች በስተቀር ተጠቃሽ እንቅስቃሴዎች ሳያስመለክተን በቀጠለው ጨዋታ ንግድ ባንኮች በሁለት ተጨማሪ አጋጣሚዎች ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው 71ኛው ደቂቃ ላይ ሙዳቲር አባስ ያህያ አባሲ ያደረገውን ሙከራ ፈቱዲን ጀማል በግሩም ቦታ አያያዝ ሲያግድበት በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ተቀይሮ የገባው ክሌመንት ፍራንሲስ ምዚዜ ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ በመጠኑ ሲነቃቃ በተጨመሩ የባከኑ 6 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ያንግ አፍሪካዎች ተጨማሪ ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ክሌመንት ፍራንሲስ ምዚዜ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ክላቶውስ ቾታ ቻማ በደካማ አጨራረስ አባክኖታል። ጨዋታውም በያንግ አፍሪካንስ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የመልሱ ጨዋታ በመጪው ቅዳሜ መስከረም 11 2017 ዛንዚባር ላይ ይደረጋል።