የአሰልጣኞች አስተያየት| የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 0 – 1 ያንግ አፍሪካንስ

በሁለተኛው ዙር የቶታል ካፍ ቻምፕዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታ በሜዳው የታንዛንያውን ያንግ አፍሪካንስን የገጠመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ሽንፈት አስተናግዷል፤ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የክለቡ ምክትል አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።


ስለ ጨዋታው

“እንደሚታወቀው ያንጋ አፍሪካንስ ትልቅ ክለብ ነው፤ በዛ ደረጃ ነበር የተዘጋጀነው። በራሳቸን መንገድ ነበር የቀረብነው ፤ ከመጀመርያው ደቂቃ ጀምሮ ኳሱን ከኃላ መስርተን ለመጫወት ነበር የሞከርነው። በመጀመርያው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ጥሩ ጅማሮዎች ነበሩ ግን በተከታታይ ወደ ኋላ የምንመልሳቸው ኳሶች ዋጋ አስከፍለውናል።እነሱ በመጀመርያው አጋማሽ የፈጠሯቸው አብዛኞቹ የጎል ዕድሎች ወደ ኋላ በሚመለሱት ኳሶች ነው፤ እሱ ዋጋ አስከፍሎናል። ሁለተኛው አጋማሽ እሱን አርመን የተሻለ ነገር ለመፍጠር ሙከራ አድርገናል፤ ነገር ግን ጅማሮ ላይ እንጂ ቀጣይነት አልነበረውም። በጨዋታው ማግኘት የሚገባንን ነገር አላገኘንም ብዬ አስባለው። በአጠቃላይ እንቅስቃሴያችን ጥሩ አልነበረም።”

ስለ ቅያሪዎቹ መዘግየት ?

“አዎ ዘግይቷል። የመቀየር ፍላጎቶች ነበሩ፤ ነገር ግን የምንጠብቃቸው ነገሮች ነበሩ። የቀየርናቸው ተጫዋቾች በማንኛውም ጊዜ ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ ናቸው ለዛም ነው ዘግይተን ቅያሪ ያደረገነው።”


ስለ መልሱ ጨዋታ

“በመልሱ በሜዳቸው ነው የምንጫወተው ትልቅ ደጋፊ አላቸው፤ ትልቅ ቡድን ነው ነገር ግን እግርኳስ ነው ለማሸነፍ ነው የምንገባው። የምንችለውን ነገር አድርገን ቀጣዩ ጨዋታ በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ጥረት እናደርጋለን።”