ባለፉት የውድድር ዓመታት በኃይቆቹ ቤት ቆይታ የነበረው ተጫዋች ወደ ምዓም አናብስት አምርቷል።
ቡድናቸውን ለማጠናከር በርከት ያሉ ዝውውሮችን በመፈፀም ለቀጣይ የውድድር ዓመት በሀዋሳ ከተማ በመዘጋጀት ላይ ያሉት መቐለ 70 እንደርታዎች ባለፉት ዓመታት በሀዋሳ ከተማ ቆይታ የነበረውን ሁለገቡን መድኃኔ ብርሃኔን የግላቸው አድርገዋል። ከሀዋሳ ከተማ ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እያለው ከቡድኑ ጋር በጋራ ስምምነት ተለያይቶ ከቀድሞ አሰልጣኙ ዳንኤል ፀሐዬ ጋር በድጋሚ ለመሥራት ወደ መቐለ ያመራው ተጫዋቹ ባለፈው የውድድር ዓመት በግራ እና በቀኝ ተከላካይነት ለ1487′ ደቂቃዎች ኃይቆቹን ማገልገሉ የሚታወስ ነው።
የእግር ኳስ ሕይወቱ ራዕይ በሚባል የታዳጊዎች ቡድን ከጀመረ በኋላ ቀጥሎ የደደቢት ታዳጊ ቡድንን በመቀላቀል በ2009 ወደ ዋናው ቡድን አድጎ አሳዳጊ ክለቡን ለሁለት ዓመታት ማገልገል የቻለው ወጣቱ ተከላካይ ከዚያ ቀደም በስሑል ሽረ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ሀዋሳ ከተማ መጫወት የቻለ ሲሆን ጥሩ ብቃት አሳይቶ ከእግር ኳስ ቤተሰቡ ጋር ከተዋወቀበት የ2010 የውድድር ዓመት ጀምሮ በተከላካይነት፣ በመስመር እና በአጥቂነት መጫወት የቻለ ሁለገብ ተጫዋች ነው።
የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በመቀመጫ ከተማቸው መቐለ ጀምረው ቀጥለው በአዳማ እና ሀዋሳ ቆይታ ያደረጉት ምዓም አናብስት በነገው ዕለት ውድድሩ ወደ ሚካሄድበት ድሬዳዋ ከተማ እንደሚያቀኑም ታውቋል።