አዲሷ የዲሲ ፓወር ፈራሚ ትናገራለች…..

ከቀናት በፊት ወደ በአሜሪካ ዩኤስኤል ሱፐር ሊግ ተካፋይ ለሆነው ዲሲ ፓወር ፊርማዋን ያኖረችው ኢትዮጵያዊቷ አጥቂ ሎዛ አበራ ስለ አሜሪካ ቆይታዋ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርጋለች….

በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ በልዩነት ከደመቁ ተጫዋቾች መካከል የእርሷን ያህል ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የተገኘ አለ ለማለት ያዳግታል። በሀዋሳ ከተማ የጀመረው የእግር ኳስ ህይወቷ በደደቢት ፣ አዳማ ከተማ እያለ ከሀገር ተሻግራም በስዊዲኑ ክለብ ኩንግስባካ እንዲሁም በማልታው ክለብ ቢርኪርካራ በግቦች የታጀቡ የተሳኩ ጊዜያትን አሳልፋለች።

ቀጥላም ዳግም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥሩ ዓመታትን አሳልፋለች። በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እና በዓመቱ ምርጥ ተጫዋችነት በተደጋጋሚ ስሟን በማፃፍ ተሸላሚ የነበረችው የ26 ዓመቷ አጥቂ ሎዛ አበራ ከስምንት ወራት በፊት በሙከራ በUSL ሊግ ለሚካፈለው አማተር ክለብ ቨርጂኒያ ማራውደርስ ካሳለፈች በኃላ ከቀናቶች በፊት ደግሞ የUSL ሱፐር ሊግ ተካፋይ ወደ ሆነው ከተመሠረተም አንድ ዓመት ላስቆጠረው ዲሲ ፓወር እግር ኳስ ክለብ የሁለት ዓመት ኮንትራትን ፈርማ ክለቡን በይፋ ተቀላቅላለች። በአዲሱ ክለቧም የመጀመሪያ ጨዋታዋን ባሳለፍነው ሳምንት ተቀይራ በመግባት ከውናለች።

ሶከር ኢትዮጵያም የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት በመሆን ከአሜሪካ እግር ኳስ ጋር መተዋወቅ ከቻለችው አጥቂ ጋር ስለ አሜሪካ ቆይታዋ እና ስለ ቀጣይ ዕቅዶቿ ቆይታን አድርጋለች ፤ ቆይታችንም እንደሚከተለው ቀርቧል።

ስምንት ወራት ካስቆረጠው የአሜሪካ ቆይታሽ እንጀምር…?

“አጠቃላይ ወደ አሜሪካ ከመጣሁ ስምንት ወር ሆኖኛል ስመጣ ለሙከራ ነበር የመጣውት ያንን ሙከራ ከመዝሙረ ዳዊት ጋር በመሆን ነው የሞከርኩት በዚያ ሙከራ ወቅትም ጥሩ ነገር በማሳየቴ ቨርጂኒያ ማራውደርስ ክለብ ተቀላቀልኩ። በማራውደርስ ቆይዬ በጋ ላይ በአንድ አጋጣሚ አንድ ጨዋታ ላይ የተመለከቱኝ የዲሲ ፓወር ክለብ አሰልጣኞች የመለመሉኝ ፤ ከዚያም እኔን ጨምሮ ከእኛ ቡድን ለአራት ልጆች የሙከራ ዕድል ሰጡን። ዋና አሰልጣኛችን ጄን እርሷ ናት ጥቆማውን ያደረገችው ፤ ከዚያ በኋላ በሙከራ አራታችን ታየን ልክ እንደኛም ከተለያየ ቡድን የመጡ ሌሎች ተጫዋቾች ነበሩ።”

“እኛ የነበርንበት ዩኤስ ኤል ሊግ ይባላል ሰሚ ፕሮፌሽናል ሊግ ሆኖ በሴቶች ሁለተኛ ሊግ ማለት ነው ይሄ ሊግ ምንድነው ዋናው ስራው ፕሮፌሽናል ተጫዋች መሆን እና ህልማቸውን ማሳካትም ለሚፈልጉ መንገዱን የሚያመቻች ሊግ ማለት ነው። ተጫዋቾች በዚህ ሊግ ላይ ታይተው ወደ ፕሮፌሽናል ቡድን እንዲገቡ ይደረጋሉ። እኛም በአሰልጣኛችን ምክረ ሃሳብ
ወደ ዲሲ ፓወር ለሙከራ ሄድን ከእኛ ቡድን ከሄድነው ውስጥ ሁለት ልጆች ተወሰድን ማለት ነው።በዚህም አማካይነት ወደዚህ ክለብ ገባሁኝ አሁን ዲሲ ፓወርን ተቀላቅዬ የውድድር ዘመኑን ጀምረናል አራተኛ ጨዋታችንን አድርገን ነበር እኔም የመጀመሪያ ጨዋታዬን አድርጌያለሁ።”

ብዙ ስኬቶችን አይተሻል በሀገር ውስጥ ወደ አውሮፓም ጎራ ብለሽ የመጫወት ዕድሉም ነበረሽ አሁን ደግሞ ከፍ ወዳለሁ የአሜሪካ ሊግ አምርተሻል አቀባበሉ ምን ይመስል ነበር…?

“ዲሲ ፓወር በጣም የተደራጀ ቡድን ነው ፣ ሲቀጥል እዚህ ዲሲ ፣ ቨርጂኒያ እና ሜሪላንድ ያሉ ስቴቶችን የሚወክል እና መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገ ቡድን ነው።ዲሲ ዩናይትድ በወንዶቹ ዲሲ ፓወር ደግሞ በሴቶቹ አንድ ናቸው እንዳልኩህ ከዚህ በፊትም የነበሩኝ ልምዶች ነበሩ ፤ በአውሮፓም ከነበረኝ ልምድ ይሄ እጅግ በጣም የላቀ ነው።በብዙ መልኩ ከአውሮፓው ይለያል የሊግ ደረጃው ፣ ጥንካሬውም እንዲሁም በአወቃቀር ደረጃም ልዩነቶች አሉ። እዚህ የተጫዋቾቹ አቅምም በጣም አሪፍ ነው እኔ በግሌ በጣም ብዙ ነገር እየተማርኩኝ ነው በጣም ብዙ ነገር ያሻሻልኩት ያሳደኩት ነገር አለ። በአዕምሮም ሆነ በአካል ብቃት ብዙ ነገሮችን እንዳሳድግ እና እንድጨምር አድርጎኛል እና ጥሩ ጅማሬ ላይ ነው ያለነው ፤ በዚያ ላይ ዲ ኤም ቪ አካባቢ ላይ መሆኑም ብዙ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ለማግኘትም ድጋፍ ለማግኘትም አሪፍ ነው።”

ከፍ ወዳለ ሊግ አምርተሽ የሁለት ዓመት ውል እንደፈረምሽ ይታወቃልና እስቲ ስለ ኮንትራትሽ ዝርዝር ብትንገሪን…?

“ኮንትራቱ የሁለት ዓመት ኮንትራት ነው ፣ በዚህ የሁለት ዓመት ኮንትራት ውስጥ በተለይ ይሄኛው 2024/25 የመጀመሪያው ዓመት በማሳየው ብቃት እና አቅም ተመስሮቶ የሚሻሻሉ ነገሮች ይኖራሉ። በዋናነት በተለይ የእኔ አቅም ጋር ከእኔ ብቃት መጨመር ጋር ተያይዘው የሚያድጉ ብዙ ጥቅማጥቅሞች የተካተቱበት ውል ነው። እዚህ ዲ ኤም ቪ ላይም እንደሚታወቀው በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደመኖራቸው ብዙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎችም እንደመኖራቸው እኔም ህልሜን ከመኖር ባለፈ ሌሎችም ተጫዋቾችም እኔ ባገኘሁት ዕድል ተስፋ ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ። ኮንትራቱ ላይ ይሄ ነገር ባይኖርም ግን ሎዛ አበራ እዚህ ሊግ ላይ በምታሳየው አቅም ብዙ ክለቦችም ይሁኑ የእኛም ክለብ የእኛን ሀገር ተጫዋቾች የማየቱ ዕድላቸው እየሰፋ ይመጣል ብዬ አምናለሁ።”

“እዚህ አሜሪካ ሊግ ላይ USL የሚባለው ሊግ ላይ ለምሳሌ እነ ናኦሚ ግርማ የሚጫወቱበት ሊግ ላይ ኦርላንዶ ፕራይድ የምትጫወተው ባርባራ ባንዳ ካየሀት እሷ በፈጠረችው አቅም እሷ በፈጠረችው ተፅዕኖ ከእርሷ በኋላ ሁለት የዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ኦላንዶ ፕራይድን ተቀላቅለዋል ሌሎችም አሉ እዚህ የናይጄሪያ ተጫዋቾች ፣ የደቡብ አፍሪካ ተጫዋቾች ባለፈው እኔ በብሔራዊ ቡድን ተቃራኒ ሆኜ የገጠምኳት ኦሽዋላ ሳትቀር እዚህ አሜሪካ ሊግ ላይ ነው የምትጫወተው እና የእነርሱ ተፅዕኖ አሁን ላይ ብዙ የአፍሪካ ተጫዋቾች ባልተለመደ መልኩ በ2024 በጣም ብዙ የአፍሪካ ተጫዋቾች አሜሪካ ሊግ ላይ እየተጫወቱ ነው። ይህ ሁሉ መሆን የቻለው አንድ ተጫዋች ይመጣል ያ ተጫዋች ከታየ በኋላ ክለቦች አሰልጣኞች ወኪሎች ተጫዋችን ይፈልጋሉ ስለዚህ በዚያ ሰዓት ተጫዋቾቹ እነዚህን ነገሮች እየሰሩ ለብዙ ልጆች ዕድል እየፈጠሩ ነውና ያ ደግሞ የእኔ ትልቁ የሁልጊዜ ህልሜ ስለሆነ እንደዛ የሚሆንበት ዕድል ሰፊ ነው ብዬ ከፈጣሪ ጋር አስባለሁ።”

ከባለቤትሽ ዮሐንስ ፍቃዱ ጋር አብራችሁ ነበር የምትኖሩት አሁን ግን ለስምንት ወራት ተራርቃችሁ ነው ያላችሁ እና በቀጣይስ አብሮ ለመኖር ወደዚህ የማምጣት ዕቅድ ይኖርሽ ይሆን…?

“ከቤተሰብ ጋር በዚህ ሁኔታ መራራቅ ከባድ ነው ፤ ባለቤቴ እንደምታውቀው ለስፖርት በጣም ቅርብ የሆነ ሰው ነው የእኔን ሙያ ደግሞ በጣም የሚያከብር የሴቶችን እግር ኳስ የሚከታተል እና የሚወድ ሰው ነው።ስለዚህ እሱ በዚህ መልኩ መሆኑ እኔን አግዞኛል በተለይ ጫና አያደርግብኝም ህልሜን እንድኖር አላማዬን እንዳሳካ በብዙ የሚደግፈኝ ሰው ነው ፤ በዚሁ አጋጣሚም በጣም ላመሰግነው እፈልጋለሁ ሁሌም ቢሆን ጫናዎችን እርሱ ተሸክሞ እኔ የእኔን ስራ ብቻ እንድሰራ የሚያደርገኝ ሰው ነው ስለ እርሱም በጣም እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ እንደዚህ አይነት ሰው ስለሰጠኝ ግን እንደጠየከኝ ቤተሰብ ከሁሉም ነገር በላይ ስለሆነ አንድ ላይ መሆናችን ግድ ነው ስለዚህ በቀጣይ እነዚህ ነገሮች ይሆናሉ።”

ባሳለፍነው አርብ የመጀመሪያ ጨዋታሽን ሮርት ላውደርዴል ከተባለ ቡድን ጋር በአዲሱ ክለብሽ ተቀይረሽ በመግባት አድርገሻል እና የመጀመሪያው ጨዋታሽ እንዴት ነበር…?

“በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር በዕርግጥ ቡድናችን ሁለት ለባዶ ተሸንፈናል ግን በሜዳችን የመጀመሪያ ጨዋታ ነበረ በጣም ድባቡ ደስ ይል ነበረ ደጋፊዎች ነበሩ ብዙ ሰው ነበር እና ቤተሰቦች ጓደኞች ደጋፊዎች በነበሩበት ደስ በሚል ሁኔታ ስለተጫወትን እኔ ደስተኛ ነኝ ተቀይሬም ገብቼ ሰላሳ አምስት ደቂቃ ተጫውቻለሁ። በግሌ በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር ያሳየሁት የጎል ዕድሎችንም መፍጠር ችዬ ነበር በጨዋታው በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ የተሻለ ነገር ለመስራት ሞክሬያለሁ ይሄንኑ እያሳደኩ መቀጠል በቀጣይ ጨዋታዎች በሚሰጠኝ ዕድል የተሻለ ነገርን እሰራለሁ ብዬ አምናለሁ።”


በመጨረሻም የምታስተላልፊው መልዕክት ምስጋናም ካለ…?

“በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያዊያን የስፖርት ፌስቲቫል ላይ በክብር እንግድነት የጋበዙኝን ጨምሮ በእግር ኳስ ህይወቴ ውስጥ ያገዙኝን የረዱኝንም ሰዎች ቤተሰቦቼን ባለቤቴን እዚህም ደግሞ አብረውኝ ያሉትን ቤተሰቦቼን ጓደኞቼን በጣም ላመሰግን እወዳለሁ ፤ ከዚያ ውጪ እዚህ ከመጣሁኝም በኋላ ኢትዮጵያም እያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሸንን ጨምሮ አቶ ባህሩ ጥላሁንን ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ፣ ከዛ መዝሙረዳዊትን ፣ ከእሱ ጋር ያገናኘኝ ፍፁምን ፣ አሰልጣኝ ብርሃኑ ፣ አሰልጣኝ ፍሬውን ቀደም ብዬ የነበርኩበትን ማራውደርስ ክለብ ፣ የግል አሰልጣኜ ረድኤት ብርሀኑ እና ጆ ማሞ ካቻን ከዛ ውጪ በምክርም አይዞሽ እያሉ ያገዙኝን እዚህም ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ሆነ ሀገር ቤትም ያሉትን ኢትዮጵያዊያንን በብዙ አመሰግናቸዋለሁ። በዚሁ አጋጣሚም ለመላው ኢትዮጵያዊያን መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን
እመኛለሁ።”