ሲዳማ ቡና የሦስት አምበሎቹን ዝርዝር አሳውቋል

በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመሩት ሲዳማ ቡናዎች ሦስት የቡድን አምበሎቻቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ይፋ አድርገዋል።

ጠንከር ካለው የክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር በኋላ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በሀዋሳ ታደሠ እንጆሪ ሆቴል ከትመው ልምምዶቻቸውን ሲሠሩ የከረሙት በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ፊት አውራሪነት የሚመሩት ሲዳማ ቡናዎች ለ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዝግጅታቸውን አገባደው ከቀናት በፊት ወደ ድሬዳዋ ከማምራታቸው በፊት በዛሬው ዕለት ምሽት ቡድኑን በአምበልነት የሚያገለግሉ ሦስት ተጫዋቾችን በመምረጥ ለሶከር ኢትዮጵያ በላኩት መረጃ አመላክተዋል።

ከዳሽን ቢራ ጋር በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትውውቁን ያደረገው የመሐል ተከላካዩ ያሬድ ባየህ አዲሱ የቡናማዎቹ አምበል ሆኗል። በፋሲል ከነማ እና ላለፉት ሁለት ዓመታት ባገለገለበት የቀድሞው ክለቡ ባህር ዳር ከተማ የመሪነት ሚናውን ሲወጣ የምናውቀው የኋላ ደጀኑ በአዲሱ ክለቡ ሲዳማ ቡና ቤትም የቡድኑ የተጫዋቾች እና የሜዳ አለቃ ሆኖ ተመርጧል። ሌላኛው ቡድኑን በሁለተኛ አምበልነት እንዲያገለግል የተመረጠው ከሀዋሳ ከተማ እግር ኳስን የጀመረው እና ከአዳማ ከተማ በመቀጠል ወደ ሲዳማ ቡና የተጠናቀቀውን ዓመት አምርቶ ክለቡን በዋና አምበልነት መርቶ የነበረው ደስታ ዮሐንስ በአዲሱ ምደባ ሁለተኛው የቡድኑ አምበል ሲሆን የቀኝ መስመር ተከላካይ የሆነው የቀድሞው የደቡብ ፓሊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋች ብርሃኑ በቀለ በበኩሉ ሦስተኛው የክለቡ አምበል ሆኖ ተመርጧል።