የ2017 የውድድር ዘመን የአርባምንጭ ከተማ አምበሎች እነማን እንደሆኑ ሶከር ኢትዮጵያ መረጃውን አግኝታለች።
ከአንድ ዓመት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሱት አርባምንጭ ከተማዎች ሊጉ ከመጀመሩ በፊት አምበሎቻቸውን አሳውቀዋል። በዚህም መሰረት የመሃል ተከላካዩ አበበ ጥላሁን የቡድኑ ቀዳሚ አንበል መሆኑ ሲረጋገጥ በ2004 አርባምንጭ ከተማ ዳግም ወደ ሊጉ ሲመለስ ትልቅ አበርክቶ የነበረው ተጫዋቹ በተለያዩ ክለቦች የእግርኳስ ሕይወቱን ከገፋ በኋላ በ2015 ዳግም ቡድኑን በመቀላቀል በአንበልነት ሲመራ መቆየቱ ይታወሳል።
ሁለተኛ አንበል ሆኖ በአሰልጣኝ በረከት የተመረጠው አጥቂው አህመድ ሁሴን ነው። ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲመለስ 18 ጎሎችን በማስቆጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው አጥቂው ሲመረጥ ሦስተኛ አንበል እንዲሆን አካሉ አቲሞ እንዲሆን መመረጡ ታውቋል።
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና በመስከረም 10 ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የመጀመርያ የሊግ ጨዋታውን የሚያከናውነው ክለቡ ከትናንት በስቲያ የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ በተገኙበት ሽኝት ተደርጎለት በትናንትናው ዕለት ውድድሩ ወደ ሚካሄድበት ድሬዳዋ ከተማ አቅንቷል።