ከ1630 ቀናት በኋላ ዳግም የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ለማድረግ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታ አምበሎቻቸው ታውቀዋል።
ቀደም ብለው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬን ቅጥር በመፈፀም ወደ ዝውውር የገቡት እና በርከት ያሉ ዝውውሮች በመፈፀም በመቐለ፣ አዳማ እና ሀዋሳ ከተሞች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸው ያከናወኑት መቐለ 70 እንደርታዎች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ በፊት የቡድኑ አምበሎች ለሶከር ኢትዮጵያ ይፋ አድርገዋል።
በዚህም መሰረት ላለፉት ስድስት ዓመታት በክለቡ ቆይታ የነበረው እና ከዚህ ቀደም ከቡድኑ አምበሎች አንዱ የነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ አንተነህ ገብረክርስቶስ የቡድኑ ተቀዳሚ አምበል ሲሆን ፤ በ2010 ቡድኑን ተቀላቅሎ እስከ 2011 አጋማሽ ቡድኑን በማገልገል ባለፈው የውድድር ዓመት በድጋሜ ወደ ክለቡ ተመልሶ መጫወት የጀመረው የቀድሞ የስሑል ሽረ አምበል የሆነው የመሀል ተከላካዩ ዮናስ ግርማይ ሁለተኛው ተመራጭ ሆኗል።
እንዲሁም ከዚህ ቀደም የክለቡ የከፍተኛ ሊግና የፕሪምየር ሊግ ስኬቶች ትልቅ ድርሻ የነበረው በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው አማካዩ ያሬድ ከበደ የቡድኑ ሶስተኛ አምበል ሲሆን አዲስ ፈራሚው የቀድሞ የደደቢት፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማ አማካይ ያብስራ ተስፋዬ የቡድኑ አራተኛ አምበል መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።