የ19 ክለቦች ሩጫ በ2017….! – ክፍል 1

    በ38 የጨዋታ ሳምንታት 19 ክለቦችን የሚያፋልመው የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የፊታችን ዓርብ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በይፋ ይጀምራል ፤ እኛም ከውድድሩ ጅማሮ አስቀድሞ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ምን ምን ጉዳዮችን ይጠበቃሉ ስንል ተከታዩን ፅሁፍ አሰናድተናል።

    👉ከ16 ዓመታት በኋላ ፕሪምየር ሊጉ ከፍ ባለ የተሳታፊዎች ቁጥር ይመለሳል…..

    የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የፊታችን ዓርብ መስከረም 10/2017 በይፋ በድሬዳዋ አለም አቀፍ ስታዲየም ሲጀመር ባለፉት ዓመታት በ16 ክለቦች መካከል ብቻ ይደረግ የነበረው ውድድሩ በያዝነው ዓመት ግን ተጨማሪ ክለቦችን በማካተት በ19 ክለቦች መካከል እየተደረገ ለ38 የውድድር ሳምንታት የሚይቆይ ይሆናል።

    በሚሊኒየሙ መባቻ 25 ክለቦችን ተሳታፊ ካደረገ በኃላ በ2002 የውድድር ዘመን 18 ክለቦችን አሳትፎ የነበረው ፕሪምየር ሊጉ የትግራይ ክልል ተወካይ የሆኑ ሦስት ክለቦችን መመለስ ተንተርሶ ከ16 ዓመታት በኋላ ቁጥሩ ከፍ ያለ ተሳታፊ ክለቦችን አቅፎ ውድድሩ የሚጀምር ይሆናል።


    👉ባለውለታ የነበሩት የዩኒቨርሲቲ ሜዳዎች ያበቃላቸው ይሆን…?

    የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሱፐር ስፖርት የቀጥታ ስርጭትን ካገኘበት የ2013 የውድድር ዘመን ጀምሮ የሊጉ ውድድር ከቀመው ፎርማት በተለየ በተወሰኑ ከተማዎች ወድድሩ እየተካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል ፤ ለዚህም የሊጉ አስተዳዳሪ አካል የዩኒቨርሲቲ ሜዳዎችን ከተመራጭ መዳረሻዎቹ መካከል እንደነበሩ ይታወቃል።

    ከጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የጀመረው የትምህርት ተቋማትን የሜዳ አበርክቶ በመቀጠል ሀዋሳ አልፍ ሲልም የአዳማ ዩኒቨርስቲ ሜዳዎች ሊጉ ሲከወንባቸው የተመለከትናቸው ስፍራዎች ነበሩ ፤ ታድያ እነዚህ የዩኒቨርስቲ ሜዳዎች ግን ዘንድሮ ውድድር ላይደረግባቸው እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።

    የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መዝጊያ በነበረው የሀዋሳው የዕራት ግብዣ ላይ ለክለቦች እና ለከተማ አስተዳደሮች ከአሁን በኋላ ሜዳዎችን ስሩ በዩኒቨርስቲ ሜዳዎች ላይ ከተማሪ ጋር ስለማንጋፋ ውድድር በእነኚህ ሜዳዎች ላይ አናካሂድም ማለታቸውን ተከትሎ አራት ዓመታትን በተከታታይ ውድድር ያስተናገዱት የሀዋሳ እና አዳማ ዩኒቨርስቲ ሜዳዎች ዘንድሮ ውድድር የማስሀናገዳቸው ጉዳይ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብተዋል።

    የሊጉ የቦርድ ሰብሳቢ ይህንን ንግግር ይናገሩ እንጂ ከድሬዳዋ ስታዲየም ውጪ የተሰናዳ ሜዳ አለመኖሩን ተከትሎ በቀጣይ እኚህ ሜዳዎች ወድድር ያስተናግዳሉ ወይስ አክሲዮን ማህበሩ በቃ ይፀናል የሚለው ይጠበቃል።

    👉ሰባት ክለቦች በአዳዲስ አሰልጣኞች ይቀርባሉ…

    በ19 ክለቦች መካከል የሚደረገው የዘንድሮው ውድድር በዓመቱ መጨረሻ አምስት ወራጅ ክለቦች የሚለዩበት ዓመት ከመሆኑ አንፃር በርከት ያሉ አሰልጣኞች የሚፈተኑበት ዓመት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

    በፕሪምየር ሊጉ ላይ ባሳለፍነው ዓመት ከነበሩ አሰልጣኞች መካከል አስራ ሁለቱ ከነበሯቸው ክለቦች ጋር አብረው የሚቀጥሉ ሲሆን ቀሪዎቹን አራት ክለቦች በተጨማሪነትም የትግራይ ክልሎቹን ሦስት ክለቦች ጨምሮ ሰባቱ በአዳዲስ የአሰልጣኞች እየተመሩ ወድድራቸውን ይከውናሉ።

    ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም የተመለሱት መቐለ 70 እንደርታ ፣ ወልዋሎ እና ስሑል ሽረን ጨምሮ ወልቂጤ ከተማ ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዳማ ከተማ እና አዲስ አዳጊው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአዳዲስ አሰልጣኞች ሊጉን የሚጀምሩ ሲሆን እነዚሁ አሰልጣኞች በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከአዲሶቹ ክለቦቻቸው ጋር እንዴት ይዘልቃሉ የሚለው ጉዳይ አጓጊ ሆኗል።

    👉አስገዳጁ መመርያ ወደ ሊጉ ያመጣቸው አዳዲስ ፊቶች…

    የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ያስጠናውን ጥናት መሠረት በማድረግ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ሁሉም ክለቦች በተቀመጠው የበጀት ጣሪያ ገደብ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ መወሰኑን ተከትሎ አንዳንድ ክለቦች በሊጉ ላይ ያልተመለከትናቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች በአነስተኛ ወርሃዊ ደሞዝ ወደ ክለባቸው ሲያስመጡ ተመልክተናል።

    በቀደመው ጊዜ የሊጉ ክለቦች በሊጉ እየተጫወቱ ከሚገኙ ተጫዋቾች ውጭ ማስፈረም ዕርም ያሉ ቢመስልም ምስጋና ለአዲሱ አስገዳጅ መመሪያ ይሁንና የተወሰኑት ክለቦች ከፕሪምየር ሊጉ ባሻገር ከከፍተኛ ሊጉ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በመያዝ በፕሪምየር ሊጉ ሊያስተዋውቁን ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።

    👉ከ50% በላይ ተጫዋቾቻቸውን ያጡ ክለቦች…

    በአዲሱ የክለቦች የዝውውር መመርያ መሰረት የተወሰኑ ክለቦች መመርያውን ተግባራ ባደረገ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የተወሰኑት ክለቦች ግን ይህን አሰራር በጣሰ መልኩ ስለመንቀሳቀሳቸው ስሞታ እየቀረበባቸው ይገኛል።

    መመሪያውን ለመከተል ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩት እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ፋሲል ከነማ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ወልቂጤ ከተማ
    እና ኢትዮጵያ ቡና በቡድናቸው ውስጥ የነበሩ ወሳኝ ተጫዋቾችን ለማቆየት ሳይችሉ ሲቀሩ በዚህም እነዚሁ ክለቦች የቡድን ስብስባቸው ከአምናው አንፃር ከ50% በሚልቅ መልኩ በአዲስ ለመቀየር ተገደዋል።

    በስብስብ ደረጃ ከዓመት ዓመት የጅምላ ቅየራ ለሀገራችን እግር ኳስ አዲስ ልምምድ ባይሆንም እነዚሁ ክለቦች በለቀቁባቸው ተጫዋቾች ምትክ ያመጧቸው ተጫዋቾች የጥራት ደረጃ ታሳቢ ካደረግን ምናልባት እነዚህ ክለቦች በተወሰነ መልኩ ሊቸገሩ የሚችሉበት እድል እንደሚኖር ይገመታል።