የ19 ክለቦች ሩጫ በ2017….! – ክፍል 2

በአዲሱ የውድድር ዘመን በሚጠበቁ ጉዳዮች ዙርያ ያሰናዳነው ፅሁፍ ሁለተኛ ክፍልን እነሆ።

👉በዝውውሩ የነቃ ተሳትፎን ያደረጉ ክለቦች..

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት
ሁሉም ክለቦች ራሳቸውን ለማጠናከር ጥረቶችን ያደረጉ ቢሆን የተወሰኑ ክለቦች እያሳለፉ የሚገኙት የዝውውር መስኮት በልዩነት የሚነሳ ነው።

ከታችኛው ሊግ ያሳደጉትን በርካታ ተጫዋቾችን የለቀቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በምትኩ ጠንካራ ዝውውሮችን የፈፀመ ሲሆን ሲዳማ ቡናም በክረምቱ እጀግ የላቁ ዝውውሮችን ከፈፀሙ ክለቦች ቀዳሚው ነው።

በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማ ፣ አርባምንጭ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና መቐለ ከተማ በቁጥር ከፍ ያለ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ያዘዋወሩ ሲሆን አምና ለሊጉ ክብር እስከ መጨረሻው ሲፎካከሩ የቆዩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል የነበራቸውን ስብስብ በአመዛኙ በማቆየት የተወሰኑ አዳዲስ ፊቶችን ብቻ ጨምረዋል።

ሌላኛው ትኩረት የሚስብ የዝውውር መስኮትን እያሳለፉ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ወደ ቀደመው ዘመን ፊታቸውን በማዞር በርከት ያሉ የቀድሞ ተጫዋቾቻቸውን ወደ ስብስባቸው መልሰዋል።

👉የካሳዬ አራጌን ውል የደገመው ይታገሱ እንዳለ

በእግር ኳሷችን ውስጥ እጅግ የገነገነው የቅርብ አሳቢነት አባዜ ብዙ መገለጫዎች ሲኖሩት አንዱ ማሳያም ከሁለት ዓመት የማይዘሉ የውል ስምምነቶች ናቸው።

ነገርግን ይህን እሳቤ የሰበሩ የተወሰኑ እንደ ብርቅ የሚታዩ ስምምነቶች በአንዳንድ አጋጣሚዎች ተመልክተናል በተለይ ኢትዮጵያ ቡና ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህን ለማድረግ ሲጥር አስተውለናል ፤ በወቅቱ ኢትዮጵያ ቡና ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የአራት ዓመት ኮንትራት መስጠቱ አይዘነጋም።

ታድያ ድሬዳዋ ከተማም ይህን አሰራር ደግሟል ፤ ድሬዳዋ ከተማዎች አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን ለቀጣዩቹ አራት ዓመታት በምስራቁ ክለብ የሚያቆየውን ውል በማሰር የአሰልጣኝ ካሳዬን ታሪክ ደግሟል።

👉በ2017 በርካታ የውጪ ተጫዋቾች በሊጋችን…

የሀገሪቱን እግር ኳስ የበላይ አካል በክረምቱ ካሳለፈው ውሳኔዎች አንዱ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች በስብስባቸው መያዝ የሚችሏቸው የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ቁጥር እንዲያሳድግ የፈቀደበት አንዱ ነበር።

በዝውውር መስኮቱ አጋማሽ ላይ የተወሰነው ይህ ውሳኔ ብዙዎችን ያነጋገረ ነበር ፤ ታድያ ይህን የሰሙት ክለቦች ውለው ሳያድሩ በርካታ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው እየቀላቀሉ ይገኛል።

በአማካይ አንድ ክለብ ሁለት ያህል የውጪ ተጫዋቾችን በአሁኑ ሰዓት በማስፈረም ላይ የሚገኙ ሲሆን ዘጠኝ ክለቦች በአንፃሩ ግቦቻቸውን በውጪ ዜጋ ሲያስጠብቁ ቀሪዎቹ ክለቦች ደግሞ በሀገር ውስጥ የግብ ዘብ የሚጠቀሙ ይሆናል።

መቐለ ፣ አርባምንጭ ፣ ወልዋሎ ፣ ሽረ ፣ ሀድያ ፣ ኢትዮጵያ መድን ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ መቻል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን በስብስባቸው ሦስት እና ከሦስት በላይ የውጪ ተጫዋቾችን ያካተቱ ክለቦች ሲሆኑ ወልቂጤ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ እና አዳማ አዲስ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር የውጭ ተጫዋቾችን ለማካተት ዕቅድ እንደሌላቸው ሰምተናል።


👉አዳዲሶቹ መመሪያዎች በፋይናንስ የተንገዳገዱትን ክለቦቻችንን ያድናቸው ይሆን …

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ዘንድሮ ካደረጋቸው መልካም ተግባራት መካከል ክለቦች በተሻለ መንገድ እንዲራመዱ የሚረዳውን የክለብ ላይሰንሲግ መመሪያን ተግባራዊ አድርጎ ክለቦች በተቀመጠው የመመሪያ መስፈርት መሠረት እየተንቀሳቀሱ የሚገኝ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሊግ አክሲዮን ማህበሩ ለክለቦች የበጀት ጣሪያን አስቀምጦ ተግባራዊ እንዲደረግ ስራዎችም እየተሰሩ ይገኛል።

በፕሪምየር ሊጉ በተደጋጋሚ ለተጫዋቾቹ ደመወዝ አለመክፈል እና ባልተከፈለ ዕዳም በየከተማዎቹ የክለቦች የተጫዋቾች ማጓጓዧ አውቶብሶቻቸው የተያዙባቸው በርካታ ክለቦች እንዳሉ ይታወቃል ታድያ እነዚህ አዳዲስ መመሪያዎች እነዚህን ቋጠሮቻቸውን ይፈቱ ይሆን የሚለውን የበርካቶች ጥያቄ ነው።

ክለቦች ዕዳ እና ውዝፍ ክፍያዎቻቸውን በአግባቡ እንዲከፍሉ የሚያስገዱ ህጎች ያቀፈውን መመሪያ ክለቦች ካለፉት ዓመታቶች ተምረው ተግባራዊ ያደርጉት ይሆን የሚለው ጉዳይ ከሚጠበቁት ዓበይት ሁነቶች አንዱ ነው።